ኢትዮጵያ የወደብ አማራጮች ያስፈልጋታል – ዓለም አቀፍ ምሁራን
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ተጨማሪ የወደብ አማራጮች ያስፈልጋታል አሉ ዓለም አቀፍ የምጣኔ ኃብት ባለሙያዎች።
በአሜሪካ ሳውዘርን ኮኔቲከት ስቴት ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ኃብት መምህራን ከፋና ዲጂታል ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጠንካራ ትብብር በመፍጠር የኢትዮጵያን የባህር በር ችግር መፍታት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የምጣኔ ሀብት መምህር ጄምስ ቶርሰን (ፕ/ር) ኢትዮጵያ አሁን የንግድ እንቅስቃሴዋን በአንድ ሀገር በኩል ብቻ እያከናወነች መሆኑን ጠቅሰው፥ ሌሎች አማራጮችም ያስፈልጓታል ብለዋል፡፡
የአማራጭ ወደቦችን አስፈላጊነት ሲያስረዱም ከራስ ቁጥጥር ውጪ የሆነ ብቸኛ የንግድ መንገድ በተለያዩ ምክንያቶች ከተዘጋ ኢትዮጵያ ሊያጋጥማት የሚችለውን ትልቅ ችግር በስጋትነት ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ ተጨማሪ የወደብ አማራጮች ሊኖሯት እንደሚገባ አጽንኦት በመስጠት ቀጣናዊ ትብብርን ማጠናከር ሁሉንም የአካባቢውን ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
ምርትን ለማጓጓዝ ተመራጩና ወጪ ቆጣቢው መንገድ በባህር ማጓጓዝ መሆኑን የሚገልጹት በዩኒቨርሲቲው የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ሳሙኤል ኬ አንዶ (ፕ/ር) በበኩላቸው፥የኢትዮጵያ የወደብ ፍላጎት ድህነትን ለመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡
ለዚህም የቀጣናው ሀገራት በመተባበር ሊሰሩ እንደሚገባና የሸቀጦችን በነፃነት መንቀሳቀስ የሚችሉበትን መንገድ ሊፈጥሩ እንደሚገባ ነው ሳሙኤል ኬ አንዶ (ፕ/ር) ያስረዱት።
በዮናስ ጌትነት