በመዲናዋ የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ በ18 ዘርፎች የሚከናወነው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠናክሮ ቀጥሏል አለ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት፡፡
ከተማ አስተዳደሩ በ2017 በጀት ዓመት የበጎ ፈቃድ ሥራን ተቋማዊ በማድረግ አመርቂ ውጤቶችን አስመዝግቧል።
በየዓመቱ አያሌ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ጎልማሶች፣ በተለያዩ የሙያ ዘርፍ ያሉ ዜጎች፣ ባለሃብቶችና ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አግልግሎቶች ላይ ተሳትፈዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ በእውቀት፣ በጊዜ እና በገንዘብ ጉልህ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ እንደሚገኝም የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡
በመዲናዋ የተጀመረውን የእውቀት፣ የገንዘብና የጉልበት አስተዋጽኦ በማላቅ ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን እፎይ ለማሰኘት በጎ ፈቃደኝነትን ተቋማዊ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ቅን ልብ የተቸሩ በጎ ፈቃደኞች እያደረጉ የሚገኙት ይህ ተግባር እሳቤው አሁን ላይ በሕብረተሰቡ ውስጥ ባሕልና የኑሮ ዘይቤ ወደመሆን ደረጃ እየተሸጋገረ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ 18 ቢሊየን ብር ያህል የሚተመን ሃብት በእውቀት፣ በጊዜና በአይነት ለከተማዋ ማበርከት መቻሉ ተጠቅሷል፡፡
በአሁኑ ወቅትም የ90 ቀናት የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸው ነው የተገለጸው፡፡
በ2017 በጀት ዓመት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለተሳተፉ አካላት ምስጋና ያቀረበው ጽ/ቤቱ ÷ነዋሪዎች በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትም በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል፡፡