Fana: At a Speed of Life!

የኢባትሎ አመራሮች እና ሰራተኞች ችግኝ በመትከል ዐሻራቸውን አኖሩ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ (ኢባትሎ) አመራሮች እና ሰራተኞች በአንድ ጀንበር አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ችግኝ በመትከል ዐሻራቸውን አኑረዋል።

በሸገር ከተማ ገላን ክፍለ ከተማ በገላን ወደብ እና ተርሚናል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በተካሄደው የችግኝ ተከላ ሥነ ሥርዓት የተቋሙ አመራሮች እና ሰራተኞች ተሳትፈዋል።

የኢባትሎ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት÷ ተቋሙ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ንቁ ተሳትፎ ሲያደርግ ቆይቷል።

በዚህም ከድህነት ለመውጣት እና በምግብ እራስን ለመቻል በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት የበኩሉን እየተወጣ ነው ብለዋል።

እንደ ሀገር በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በተከናወኑ ተግባራት ዓለም አቀፍ እውቅና መገኘቱን አንስተው፤ የኢትዮጵያ ተሞክሮ ለሌሎች ሀገራት አረዓያ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን አረንጓዴ በማልበስ የበለጸገች ሀገር  እንገነባለን ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ ተቋማቸው የአረንጓዴ ዐሻራ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

ከችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ በተጨማሪ የተቋሙ አመራሮችና ሰራተኞች ደም በመለገስ እና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጥተዋል።

በዘመን በየነ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.