Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች ነው – ዲፕሎማቶች እና የውጭ ባለሀብቶች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ አማካኝነት በአካባቢ ጥበቃ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች እና የተሻለ ነገን እየገነባች ነው አሉ ዲፕሎማቶች እና የውጭ ኢንቨስተሮች።

የቻይና ኤምባሲ እና የውጭ ኩባንያ ሃላፊዎች በሸገር ከተማ ፉሪ ክፍለ ከተማ በተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ተሳትፈዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ከፍተኛ ዲፕሎማት ሊዩ ዢያዎጉዋንግ በአረንጓዴ ዐሻራ በመሳተፋቸው ትልቅ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

አረንጓዴ ዐሻራ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት እና ለቀጣይ ትውልዶች የተሻለ ጊዜን ለማምጣት እያደረገ ያለው የጋራ ጥረት እንደሆነም ተናግረዋል።

ቻይና የአረንጓዴ ልማት ትብብር አካል በመሆኗ ደስታ ይሰማታል ያሉት ከፍተኛ ዲፕሎማቱ÷ ሁለቱ ወገኖች በዘርፉ ያላቸው ግንኙነት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

ቻይና ለኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የካርበን ልህቀት መቆጣጠሪያዎች ድጋፍ እያደረገች እንደምትገኝ አመልክተዋል።

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዊም ቫንሄልፑት በበኩላቸው÷ አረንጓዴ ዐሻራ እንደ ሳፋሪኮም ያሉ ኩባንያዎች ከመንግስት ጋር  እጅ ለእጅ በመያያዝ የሚወጡት የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የግል ኩባንያዎች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ከዛሬ አልፎ ለትውልድ በሚሻገረው የአረንጓዴ ዐሻራ እና ሌሎች ኢሼቲቮች ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ስቲል ፕሮፋይሊንግ እና ቢውልዲንግ  ኩባንያ ዋና ስራ አስኪያጅ ማህዲ ዜሙቺ ÷በአረንጓዴ ዐሻራ ላይ በመሳተፉ ክብር እንደሚሰማው ገልጸው የኢትዮጵያን መንግስት ጥረት አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ የአካባቢ አየር ጥበቃን ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች እንደምትገኝ  ተረድቻለሁ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.