Fana: At a Speed of Life!

በአንድ ጀንበር አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 714 ነጥብ 7 ሚሊየን ችግኞች ተተክለዋል – ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአንድ ጀንበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 714 ነጥብ 7 ሚሊየን ችግኞች ተተክለዋል አሉ የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፡፡

ሚኒስትሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተካሄደውን የአንድ ጀንበር አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አስመልክተው ከጊዜያዊ ሁነት ክትትል ክፍል መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ጀንበር 700 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ 714 ነጥብ 7 ሚሊየን ችግኝ መተከሉን አስረድተዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ በተደረገው ርብርብ ባለፈው ዓመት የነበረው ክብረ ወሰን እንደተሻሻለ እና በዘንድሮው ዓመት ከታቀደው በላይ ማሳካት መቻሉን ገልጸው ÷ ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

በችግኝ ተከላው በሀገር አቀፍ ደረጃ 29 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉ ሲሆን÷ በ294 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ ደግሞ የችግኝ ተከላው መከናወኑን ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ስትራቴጂ ነድፋ እሰራች ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ ከልማት ዕቅዶች አንዱ አረንጓዴ ዐሻራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ታዳጊ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂ መሆናቸውን ያብራሩት ሚኒስትሩ÷ ችግሩን ለመቅረፍ ሀገራት በአረንዴ ዐሻራ ዘርፍ በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በዛሬው ዕለት ለተመዘገበው ታሪካዊ ድል የሕብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው÷ በቀሪ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩም ንቁ ተሳትፎ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.