መከላከያን ዘመኑን የዋጀ ተቋም አድርጎ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ እየተሰራ ነው – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መከላከያን ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለና ዘመኑን የዋጀ ተቋም አድርጎ ለማስረከብ በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል እና የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ጠቅላይ መምሪያዎች ቢሮዎችንና የመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምሪያ ግንባታ ሒደትን ተመልክተዋል፡፡
ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በመሰረተ ልማት ግንባታ ዘርፍ ቀጣዩን የመከላከያ ዕድገትና ዘመናዊነት ግምት ውስጥ በማስገባት በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለና ዘመኑን የዋጀ ተቋም ለማስረከብ በሚፈለገው ጥራትና ፍጥነት ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡
ለተቋሙ የተመደበውን መደበኛ በጀት ያለምንም ብክነት ጥቅም ላይ በማዋል በርካታ ዘርፈ ብዙ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ መገንባት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
ከለውጡ በፊት ፕሮጀክቶችን ጀምሮ መተው፣ የተመደበውን በጀት በአግባቡ ያለመጠቀምና ለብክነት የመዳረግ ችግሮች እንደነበሩ አስታውሰዋል።
አሁን ላይ ግን ፕሮጀክቶችን ጀምሮ መተው አይታሰብም ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ÷ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ተገንብተው ለአገልግሎት እየበቁ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ጠቅላይ መምሪያና የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ ቢሮዎች በጥራት ተገንብተው እየተጠናቀቁ እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በጉብኝታቸው ወቅት አረንጓዴ አሻራቸውን ማኖራቸውንም የመከላከያ ሠራዊት ኦንላይን ሚዲያ ዋና አዘጋጅ ሌ/ኮ ውብሸት ቸኮል ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል።
በመላኩ ገድፍ