በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ከ27 ኪሎ ግራም በላይ ጥፍጥፍ ወርቅ በቁጥጥር ስር ዋለ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በቃሊቲ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ቱሉ ዲምቱ መቆጣጠሪያ ጣቢያ በተደረገ ፍተሻ በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 27 ነጥብ 7 ኪሎ ግራም ጥፍጥፍ ወርቅ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
በቁጥጥር ስር የዋለው ጥፍጥፍ ወርቅ ከአንድ ወር በላይ ክትትል ሲደረግበት መቆየቱን የጉምሩክ ኮሚሽን የሕግ ተገዥነት ምክትል ኮሚሽነር አዘዘው ጫኔ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
ጥፍጥፍ ወርቁን በህገወጥ መንገድ በተሽከርከሪ አካል ውስጥ ደብቀው ሲያዘዋውሩ የነበሩ ሶስት ተጠርጣሪዎችና ሁለት ተሽከርካሪዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡
የኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ የአፈጻጸም ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡