የኢትዮ-ጂቡቲ የምድር ባቡር የብልጽግና ጉዟችንን የሚሸከም እንዲሆን እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮ-ጂቡቲ የምድር ባቡር ትራንስፖርት የብልጽግና ጉዟችንን የሚሸከም ተቋም ለማድረግ እየሰራን ነው አሉ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ታከለ ኡማ (ኢ/ር)።
ታከለ ኡማ (ኢ/ር) በኢትዮ-ጂቡቲ የምድር የባቡር ትራንስፖርት የሰራተኞች በዓል ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የባቡር ትራንስፖርቱ ከአድዋ ድል ማግስት የተጣለ አሻራና የቀደምት አባቶቻችን የህልምና የትግል ውጤት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያን ከዓለም ጋር የሚያገናኝ የኢትዮጵያና የጂቡቲ ሕዝቦች የትስስር መሰረተ ልማት እንደሆነ ገልጸው፥ ተቋሙ ለሁለቱ ሀገራት ልዩ ትርጉም ያለው መሆኑን አንስተዋል።
ተቋሙ የሀገሪቱ የፖለቲካ፣ ማኅበራዊ እንዲሁም የአጠቃላይ ሁኔታ አንዱ መገለጫ መሆኑን ጠቅሰው፥ የሶስት ዓመታት ስትራቴጂክ እቅድ በመቅረጽ የብልጽግና እሴቶቻችንን ለዓለም ሁሉ የምናደርስበት እንዲሆን እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮ-ጂቡቲ የምድር ባቡር በሪፎርሙ እዳውን በመክፈል ተስፋና ራዕያችንን ለማሳካት ከባይተዋርነት ወደ ባለቤትነት በሚል የልማት ቁጭት መንፈስ እየተሰራ እንደሆነም ነው የጠቆሙት።
በለይኩን አለም