ተለዋዋጭ ነባራዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረገ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራ ላይ ትኩረት ይደረጋል – ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) ተለዋዋጭ ነባራዊ ሁኔታዎችንና ሀገራዊ አቅጣጫዎችን ታሳቢ ያደረገ የሚዲያና ኩሙኒኬሽን ሥራ ላይ ትኩረት ይደረጋል አሉ።
ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአገልግሎቱ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ውይይት መድረክ ተጠናቅቋል።
ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ ነባራዊ ሁኔታዎችን መሠረት አድርጎ የኢትዮጵያን ማንሠራራት ማጽናት ላይ ያተኮረ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሥራ ትኩረት ይሰጠዋል።
በበጀት ዓመቱ የዘርፉ ዕቅድ ትኩረት ሊያደርግባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ላይ ሚኒስትሩ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በዚህም የመንግሥትን መረጃ፣ ዕቅድ፣ አፈጻጸምና ውጤት ለምልዓተ ሕዝቡ መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በመንግሥት የተያዙ ፕሮጀክቶችን ሒደት፣ ፋይዳ እና የምልዓተ ሕዝቡን ተሳትፎ ማጎልበት ላይ በትኩረት እንደሚሰራም አመልክተዋል።
ሰላምን ማጽናት፣ ስጋቶችን ቀድሞ መለየትና መተንተን፣ ልዩ ልዩ ተነሣሽነቶችን ማስረጽ፣ ብዝኃ ኢኮኖሚውንና ሪፎርሙን ማስገንዘብና ምልዓተ ሕዝቡን ማሳተፍ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የመንግሥት ሁለንተናዊ የመፈጸም ዐቅም ማደግ፣ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም በከፍተኛ ደረጃ መሻሻል፣ የሪፎርም ሥራዎች ያስመዘገቧቸው ስኬቶች እና በዲፕሎማሲ መስክ የተመዘገቡ ድሎች ለዘርፉ ሥራ መሠረቶች መሆናቸውን ነው ያብራሩት።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴዔታ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው÷ በቀጣይ በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎችን የማጋለጥ እና የመሞገት ሥራ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በሰላምና ፀጥታ፣ በኢኮኖሚ ዕድገት እና በአንኳር የልማት ሥራዎች ላይ የተመዘገቡ ውጤቶችን ለማጥላላት የሚሰራጩ አሉታዊ መረጃዎችን በትክክለኛ አሃዞች ተመሥርቶ ማረም፣ ቀድሞ ተንባይ የኮሙኒኬሽን አቅጣጫን በመከተል የአጀንዳ ብልጫ ለመውሰድ በቁርጠኝነት ይሰራል ነው ያሉት።