ታሪክ የትውልዶች የጋራ ጎዳና ነው – ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ታሪክ የትናንት፣ የዛሬ እና የነገ ትውልዶች የጋራ ጎዳና ነው አሉ።
ሚኒስትሩ ከፋና ፖድካስት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት÷ ታሪክ ትናንት ሰዎች ከኖሩበት ትምህርት ለመውሰድ፣ ዛሬን ለመረዳት እና የተሻለ ለማድረግ እንዲሁም ነገን በትክክለኛ አቅጣጫ ለመሄድ ዕድል ይፈጥራል።
ታሪክ ትናንት፣ ዛሬ እና ነገን የሚያስተሳስር ድልድይ መሆኑን ጠቅሰው÷ የሰው ልጆች በጋራ ዓላማ ለመሰለፍ የጋራ ታሪክ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የታሪክ አጻጻፍ እና መማር ማስተማር ታሪክ በአመዛኙ ፖለቲካ እንደነበር ጠቅሰው÷ ነገር ግን ታሪክ ከፖለቲካ በላይ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ ጉዳይ፣ ጥበብ እና መሰል ጉዳዮችንም ያካትታል ነው ያሉት።
ታሪክ በራሱ ችግር እንደሌለበት ገልጸው፤ ትልቁ ችግር የሚሆነው ታሪክን ለተዛባ የፖለቲካ እሳቤ መጠቀም እንደሆነ አስረድተዋል።
በመሆኑም ትናንት ላይ ተቸክሎ ታሪክን ለመማሪያ ሳይሆን ለበቀል መጠቀም፣ ዛሬ ላይ ያለውን አንድነት እና ሀገረ መንግስት የሚጎዳ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡
ታሪክን መማር፣ ማወቅ፣ መገንዘብ፣ መጠቀምም ያለብን ከትናንት መልካም ነገሮችን ለመውሰድ እና ትናንት የተሰሩ ስህተቶችን ዛሬ እንዳይደግም ለማድረግ መሆን ይገባልም ብለዋል።
መንግስት ከለውጡ በኋላ በኢትዮጵያ ያሉ የታሪክ ቅራኔዎችን ለማስተካከል የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሙን አስታውሰው÷ ኮሚሽኑ የታሪክ ቁርሾዎችን በማስተካካል የጋራ አንድነትን ለማምጣት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል።
በብርሃኑ አበራ