Fana: At a Speed of Life!

ብልጽግና ፓርቲ ሰው ተኮር ነው የሚባለው ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ይዞ ስለሚጓዝ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብልጽግና ፓርቲ ሰው ተኮር ነው የሚባለው ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ይዞ ስለሚጓዝ ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።

የብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤት አባላት ከእንጦጦ እስከ 4 ኪሎ ፕላዛ ድረስ የተሰሩ የኮሪደር ልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት÷ የአዲስ አበባ ከተማን ለማስዋብ የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎች የነዋሪዎችን ህይዎት የቀየሩ ናቸው፡፡

የኮሪደር ልማት በብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረ መሆኑን አስታውሰው፤ በአዲስ አበባም ሆነ በክልሎች ያለውን የኮሪደር ልማት ሥራ በቅርበት እየመሩት እና እየተከታተሉት እንደሆነ ተናግረዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ሰው ተኮር ነው የሚባለው ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ይዞ ስለሚጓዝ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኮሪደር ልማቱ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የሚጠቀምባቸው ምቹ ጎዳናዎችን መፍጠሩን ገልጸዋል።

ቀደም ሲል የኮሪደር ልማት ስራዎች ባለመኖራቸው የትራፊክ ችግሮች ይከሰቱ እንደነበር አስታውሰው፤ በመዲናዋ የተሰሩ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገዶች የከተማዋን የትራፊክ አደጋ የቀነሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም በእግረኛ እና የብስክሌት መንገዶች እንዲሁም በስፖርት ማዘውተሪያዎች ነዋሪዎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ህብረተሰቡ ጤናውን እየጠበቀ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም አዲስ አበባ ከነዋሪዎች ባለፈ ለጎብኝዎች የምትመች ከተማ ሆናለች ነው ያሉት፡፡

የኮሪደር ልማት ለከተሞች ልማት ትልቅ ለውጥ ያመጣ ተግባር ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኮሪደር ልማት ስራው በሁሉም ክልል ከተሞች እንዲሁም በገጠር አካባቢዎችም እየተከናወነ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.