Fana: At a Speed of Life!

ከቡንደስሊጋ ክብር በኋላ ወደ ሊጉ የተመለሰው ግራኒት ዣካ…

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቀድሞ የአርሰናል የመሃል ሜዳ ተጫዋች ግራኒት ዣካ አርሰናልን ከለቀቀ በኋላ ከጀርመኑ ክለብ ባየርሊቨርኩሰን ጋር ስኬታማ ጊዜን አሳልፏል፡፡
ከሰባት ዓመታት የአርሰናል ቆይታ በኋላ ወደ ጀርመን አቅንቶ የነበረው ስዊዘርላንዳዊው የመሃል ሜዳ ተጫዋች ግራኒት ዣካ በጀርመኑ ክለብ ባየርሊቨርኩሰን በዋንጫ የታጀበ ጊዜ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡
ለሁለት ዓመታት ያህል በጀርመን ቆይታ ያደረገው ግራኒት ዣካ ባየርሊቨርኩሰን የቡንደስሊጋውን ዋንጫ በ2023/24 የውድድር ዓመት ሲያሳካ ወሳኝ ከነበሩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነበር፡፡
ከአርሰናል የሰባት ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ጀርመን አቅንቶ የነበረው ተጫዋቹ ከሁለት ዓመታት በኋላ ለሰንደርላንድ ፊርማውን በማኖር ወደ ሊጉ ተመልሷል፡፡
ሰንደርላንድ ለ2025/26 የውድድር ዓመት ራሱን አጠናክሮ ለመምጣት አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ እየቀላቀለ ይገኛል፡፡
በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት 7ኛው የሰንደርላንድ አዲስ ፈራሚ ሆኖ ወደ ሊጉ የተመለሰው ግራኒት ዣካ ከለቡን በመቀላቀሉ ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል፡፡
የ32 ዓመቱ ተጫዋች “እኔ ያለኝን ልምድ ከቡድን አጋሮቼ ጋር በማጣመር በአዲሱ የውድድር ዘመን ሜዳ ላይ ጥሩ ነገር ለማሳየት እንሞክራለን” ሲልም ያለውን አቅምና ልምድ ሜዳ ላይ ማሳየት እንደሚፈልግ ገልጿል፡፡
ሰንደርላንድ በክረምት የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት እስካሁን ድረስ 132 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ ለተጫዋቾች ዝውውር ወጪ አድርጓል፡፡
ከ34 ቁጥር ጋር ልዩ ትስስር እንዳለው የሚነገርለት ግራኒት ዣካ÷ በሰንደርላንድ በሚኖረው ቆይታ 34 ቁጥር ማልያ የሚለብስ ይሆናል፡፡
ገና በታዳጊነቱ ወደ ባዝል የልምምድ ስፋራ ሲሄድ ይጠቀመው የነበረው የአውቶቡስ ቁጥር 34 እንደነበር ያስታውሳል፡፡
በዚህም ምክንያት 34 ቁጥር ለእሱ ልዩ ቦታ እንዳለው የሚናገረው ዣካ መጀመሪያ ፕሮፌሽናል ኮንትራቱን ሲፈርም የለበሰው ማልያ 34 ቁጥር ነበር፡፡
“34 ቁጥር በእኔ ሕይወት ውስጥ ልዩ ቦታ ስላለው አሁንም ድረስ የማልያ ቁጥሬ 34 ነው፤ ይህንን ቁጥር መቀየር አልፈልግም” በማለትም ለቁጥሩ ያለውን ልዩ ቦታ አስረድቷል፡፡
በወንድማገኝ ፀጋዬ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.