Fana: At a Speed of Life!

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምስረታ በዓል አከባበር የማጠቃለያ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 70ኛ እና የማስተማሪያ ሆስፒታሉ 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አከባበር የምስጋናና ማጠቃለያ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።

ከጥር ወር ጀምሮ የምስረታ በዓሉን በተለያዩ መርሐ ግብሮች ሲያከብር የቆየው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋን (ፕ/ር) ጨምሮ ሚኒስትር ዴኤታዎችና የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በተገኙበት ነው መርሐ ግብሩ እየተካሄደ የሚገኘው።

በመርሐ ግብሩ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ/ር) እንዳሉት÷ የምስረታ በዓል አከባበሩ ዋና ምክንያት የሀገር ባለውለታ የሆኑ ተቋማትን ጥረትና ስኬት ለማስተዋወቅ ነው።

ቀድሞ የተቋቋመው የማስተማሪያ ሆስፒታሉ ከ100 ዓመት በፊት የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል ታስቦ መቋቋሙን አስታውሰው÷ አሁን ላይ እያደገ መጥቶ የከፍተኛ ትምህርትና ስፔሻላይዝድ የሆኑ የህክምና አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከ1947 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ከመላ ሀገሪቱ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ዛሬ ላይ 22 የትምህርትና ምርምር ማዕከላት ባለቤት መሆኑንም ተናግረዋል።

ካለፉት ዓመታት ጉዞዎቹ በመነሳት የወደፊት መዳረሻዎቹን ለማቅናት ታሳቢ ያደረጉ መርሐ ግብሮችን ከጥር ወር ጀምሮ ሲያከናውን መቆየቱን በማንሳትም በቀጣይ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን በሂደት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ከፕሮጀክቶቹ መካከም በአዲስ አበባ ከተማ የምርምርና ልህቀት ማዕከል፣ የእናቶችና ህፃናት ድጋፍና ምገባ ማዕከል እንዲሁም የኩላሊት እጥበት ማዕከል ፕሮጀክትን ጨምሮ ሌሎች ዋና ዋና ፕሮጀክቶች እንደሚገኙባቸው አብራርተዋል።

ለተቋሙ ስኬታማነት ጉልህ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ተቋማትም ምስጋና አቅርበዋል።

ዩኒቨርሲቲው የገነባቸውን ህንፃዎች ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱና በቀድሞ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ከፍተኛ ሀኪሞች ስም ስያሜ ሰጥቷል።

በሙሉጌታ ደሴ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.