የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የቀድሞ ም/ዋና ዳይሬክተር በእስራት ተቀጡ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የቀድሞ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታምሩ ግንበቶ በፈፀሙት ስልጣንን ያለ አግባብ መገልገል ወንጀል ጥፋተኛ ሆነዉ በመገኘታቸዉ በእስራት እና በገንዘብ ተቀጡ፡፡
የቅጣት ዉሳኔዉን ያሳለፍዉ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ጉዳዮች ችሎት ነዉ፡፡
አንደኛ ተከሳሽ ታምሩ ግንበቶ በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የምዝገባና ቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበረ 2ኛ ጅላሉ በድሩ በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የውጪ ዜጎች ቁጥጥርና ቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክተር የነበረ ሲሆን የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 9(1) (ሀ) እና (2) ላይ የተመለከተውን አዋጅ መተላለፋቸው ተመላክቷል፡፡
አንደኛ ተከሳሽ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም በማሰብ 12 የግብፅ ዜግነት ያላቸው ግለሰቦችን ቪዛ ለማሳደስ 24 ሺህ ዶላር ቅጣት መክፈል ሲገባቸው ተከሳሹ በግንቦት 12 ቀን 2ጠ13 ዓ.ም በሰጠው ትዕዛዝ ካለባቸው የቅጣት ገንዘብ ላይ 14 ሺህ ዶላር እንዲቀነስ በማድረግ 10 ሺህ ዶላር ብቻ እንዲከፍሉ አድርጓል፡፡
ይህ 10 ሺህ ዶላርም በኢሚግሬሽን አገልግሎት ክፍያ ተመን በብሔራዊ ባንክ የምንዛሬ አገልግሎት በሚሰጥባቸው የውጭ ሀገር ገንዘብ መሆን እንዳለበት የሚገልፀውን ድንጋጌ በመተላለፍ ግለሰቦቹ በዶላር ሊከፍሉት የሚገባውን ቅጣት በኢትዮጵያ ብር ተቀይሮ እንዲከፍሉ ያደረገ መሆኑ በክሱ ተዘርዝሯል፡፡
በተጨማሪም ተከሳሾች የቻይና ዜግነት ያለው አንድ ግለሰብ የስራ ቪዛ ለማደስ 2 ሺህ 730 ዶላር መከፈል ሲገባው ተከሳሽ በሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም በሰጠው ትዕዛዝ ግለሰቡ ካለበት የቅጣት ገንዘብ ላይ 1 ሺህ 425 ዶላር እንዲከፍል በማድረጉ ሊከፈል የሚገባው 1 ሺህ 305 ሳይክፈል የቀረ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በአጠቃላይ 1ኛ ተከሳሽ የተሰጠውን ሀላፊነት ያለ አግባብ በመገልገል እና ከመመሪያ ውጪ በመስራት የቪዛ ቅጣት ክፍያዎችን በመቀነስ እና በዶላር መከፈል የሚገባቸውን ክፍያዎች 31 ሺህ 467 ዶላር ወይም 1 ሚሊየን 401 ሺህ ብር ሀገሪቷ ማግኘት የነበራትን የዉጭ ምንዛሪ ስልጣንን ያለ አግባብበ በመጠቀም እንዳይከፈል በማድረግ የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
ሁለተኛ ክስ የቀረበው በ1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ላይ ሲሆን ስድስት የቻይና ዜግነት ያላቸው ዜጎች የመኖሪያ ፈቃድ ለማውጣት ሲያመለክቱ ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደተሰጠ አድርገው ሀሰተኛ የስራ ፈቃድ መገልገላቸውን ተከትሎ ግለሰቦቹ በህግ እንዲጠየቁ እና ከሀገር እንዳይወጡ እግድ ከተሰጠ በኋላ በህገወጥ መንገድ የመኖሪያ ፈቃድ አውጥተው ከሀገር ሊወጡ ሲሉ ተይዘዋል፡፡
በዚህም የተጣለባቸው ዕግድ እንዲነሳ በመወሰን ለ1ኛ ተከሳሽ በደብዳቤ የገለፀ ሲሆን 1ኛ ተከሳሽም ግለሰቦቹ የተጣለባቸው እግድ ተነስቶ ቪዛ በአስቸኳይ እንዲሰጣቸው ያደረገ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈፀሙት ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሙስና ጉዳዮች ችሎትም ተከሳሾቹ ጥፋተኝነታቸዉ በሰዉ እና በሰነድ ማስረጃ በመረጋገጡ የቅጣት ውሳኔ አሳልፏል፡፡
በዚህም 1ኛ ተከሳሽ ታምሩ ግንበቶ በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የምዝገባና ቁጥጥር ዘርፍ የቀድሞ ምክትል ዋና ዳሬክተር በ8 አመት ፅኑ እስራት እና 1 ሺህ ብር፤ 2ኛ ጅላሉ በድሩ በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የውጪ ዜጎች ቁጥጥርና ቆንስላ ጉዳዮች የቀድሞ ዳይሬክተር በ4 አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል፡፡
በሲፈን መኮንን