Fana: At a Speed of Life!

ምርጫ ቦርድ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል የህግ ድጋፍ አግኝቷል – ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቀደም ሲል በነበረው አዋጅ ላይ ያጋጥሙ የነበሩ የአፈጻጸም እና የትርጉም ችግሮችን ለመፍታት እንዲሁም የቴክኖሎጂ አፈጻጸምን በህግ መሰረት ለመተግበር የሚያስችል የህግ ድጋፍ አግኝቷል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅን ሐምሌ 10 ቀን 2017 ዓ.ም ማጽደቁ ይታወሳል።

ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፤ ቀደም ሲል የነበረው አዋጅ ላይ የነበሩ ክፍተቶችን ለመፍታት ያለመ የአዋጅ ማሻሻያ ተደርጓል ብለዋል።

የአዋጁ ተሻሽሎ መውጣት የአሰራር ብሎም የትርጉም እና የአፈጻጸም ክፍተቶችን ለመፍታት ወሳኝ እንደሆነ ገልጸው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥቅም ላይ የዋሉ ቴክኖሎጂዎችን ለመተግበር እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የሴቶችን፣ የአካል ጉዳተኞችንና ወጣቶችን ተሳትፎ ለማሳድግ እንዲሁም የመንግስት ሰራተኞች በዕጩነት በሚቀርቡበት ጊዜ በምቹ ሁኔታ እንዲቀርቡ ለማስቻል ማሻሻያው አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ቴክኖሎጂን በመጠቀም መራጩ ማህበረሰብ በዲጂታል አማራጭ ካለበት ሆኖ የምርጫ መተግበሪያውን በማውረድ መመዝገብ ይችላል ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም መራጩ በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት በአስተባባሪዎች አማካኝነት መመዝግብ እንደሚችልም ጠቅሰዋል።

ቴክኖሎጂው ለአጠቃቀም ቀላል እና ምቹ በመሆኑ የህዝቡን የመምረጥ ፍላጎት እንደሚያሳድግ ጠቅሰው፤ በተለይ የወጣቱን የምርጫ ተሳትፎ ያጎለብታል ብለዋል፡፡

በአቤል ነዋይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.