ዝነኛዋ አንጀሊና ጆሊ በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል …
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዝነኛዋ አሜሪካዊቷ ተዋናይት አንጀሊና ጆሊ በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተገኝታ የሆስፒታሉን የስራ እንቅስቃሴውን ጎብኝታለች።
የሆስፒታሉ ረዳት ሜዲካል ዳይሬክተር ሃይደር አሕመድ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ አንጀሊና ጆሊ በሆስፒታሉ እየተሰጠ የሚገኘውን መድሃኒትን የተላመደ የቲቢ (ኤምዲአር ቲቢ) ህክምና ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን ተዘዋውራ ተመልክታለች።
በዚህም ሆስፒታሉ እየሰጠ ያለውን አገልግሎት ለማጠናከር የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ለማየትና ለመለየት መቻሏን ተናግረዋል።
ሆስፒታሉ የሚሰጠው የኤምዲአር ቲቢ ህክምና አገልግሎት መስጫ ዋርድ፣ የላቦራቶሪና ሌሎች የህክምና አገልግሎቶች ተጨማሪ ድጋፍ ከተደረገላቸው ይበልጥ ውጤታማ መሆን እንደሚችል አንጀሊና ጆሊ በጉብኝቱ ወቅት ገልጻለች።
በቀጣይ ሆስፒታሉ አስተማማኝ አገልግሎትን ለታካሚዎች እንዲሰጥ በግሎባል ሄልዝ ኮሚቴ (ጂኤችሲ) በኩል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ቃል ገብታለች፡፡
ከተዋናይነት እና የፊልም ባለሙያነት ባሻገር በሰብአዊ ድጋፍ አድራጊነቷ የምትታወቀው አንጀሊና ጆሊ ቲቢን ለማጥፋት ሆስፒታሉ በሚያደርገው ጥረት ዘላቂ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗንም ተናግራለች፡፡
በአቤል ነዋይ