ኢትዮጵያ አፍሪካውያንን በማስተሳሰር ለተሰናሰለ አህጉራዊ ቅንጅት ሚናዋን ትወጣለች – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ኢትዮጵያ በመደመር ትውልድ እሳቤ አፍሪካውያንን በማስተሳሰር ለተሰናሰለ አህጉራዊ ቅንጅት ሚናዋን ትወጣለች አሉ፡፡
12ኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ ”ከፖለቲካ እስከ ብልፅግና” በሚል መሪ ሀሳብ በጋና አክራ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
አቶ አደም ፋራህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቆራጥነት፣ በኩዋሜ ኑክሩማ አርቆ አሳቢነት፣ በነከተማ ይፍሩ ዲፕሎማሲያዊ ጥበብ አዲስ አበባ ተፀንሶ ለብዙ አፍሪካ ሀገራት የነፃነት ጉዞ ስኬታማ መሆን አስተዋጽኦ ያበረከተው የአፍሪካውያን የአንድነት እና የትብብር ጉዞ ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬም በሌላ ገፅታ እዚህ ደርሷል ብለዋል፡፡
ብልፅግና ፓርቲ አህጉራዊ ትሩፋትን መፍጠር የሚችል አዲስ የፖለቲካ ባህል እያስተዋወቀ ስለመሆኑ ገልጸው፤ ያገኘነውን ዕድል ተጠቅመን በሀገረ መንግስት ግንባታ ዙሪያ ያለንን ልምድ አካፍለናል ነው ያሉት፡፡
ለአፍሪካ ወጣቶች መፃኢ ዕድል መቃናት፣ ለዴሞክራሲ ዕውን መሆን፣ ለሰላማዊ የሽግግር ወቅቶች ስኬት፣ ለፍትሐዊ እና ተመጣጣኝ የተፈጥሮ ሀብት ክፍፍል እና ተጠቃሚነት የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ምን ሊሆን እንደሚገባ በስፋት ምክክር እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ትናንት በፀረ ቅኝ ግዛት ትግል የፈነጠቀችውን ብርሃን ዛሬም በመደመር ትውልድ እሳቤ አፍሪካውያንን በማስተሳሰር ለተሰናሰለ አህጉራዊ ቅንጅት ሚናዋን እንደምትወጣ አረጋግጠዋል።
ውሳኔዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗንም በመድረኩ አስገንዝበዋል፡፡