Fana: At a Speed of Life!

አሌክሳንደር ኢሳክና የዝውውር ውዝግቦች…

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኒውካስል ዩናይትድ የፊት መስመር ተጫዋች የሆነው አሌክሳንደር ኢሳክ በተለይም በሊቨርፑል መፈለጉን ተከትሎ ክለቡን ለመልቀቅ የገባበት ውዝግብ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡

በዚህ ክረምት የዝውውር መስኮት ሊያዘዋውሯቸው የተመኟቸውን በርከት ያሉ ተጫዋቾች በተቀናቃኞቻቸው የተነጠቁት ኒውካስል ዩናይትዶች አማራጭ ተጫዋች ሳያገኙ ተጫዋቹን የመሸጥ ፍላጎት እንደሌላቸው ሲዘገብ ቆይቷል፡፡

አሌክሳንደር ኢሳክን የግላቸው ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ሊቨርፑሎች ለኒውካስል ያቀረቡት የዝውውር ሂሳብ ውድቅ መደረጉን ተከትሎ አሻሽለው ለመቅረብ እየተዘጋጁ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

በዚህ መሃል ታድያ ተጫዋቹ ኒውካስል ዩናይትድን ለመልቀቅ እንደሚፈልግ በይፋ ለክለቡ ኃላፊዎች መናገሩ አይዘነጋም፡፡

በዚህም ምክንያት በቅድመ የውድድር ዘመን ጨዋታዎች ከኤዲ ሀው ስብስብ ውጭ የተደረገ ሲሆን፥ ከቡድኑ ተለይቶ በግሉ ልምምድ ሲሰራ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

በዚሁ አቋሙ የጸናው ስዊድናዊው አጥቂ ከዚህ በኋላ ለኒውካስል ዩናይትድ የመጫወት ምንም ፍላጎት እንደሌለው በመግለጽ ለመልቀቅ የሄደበት መንገድ ክለቡን እንዳስቆጣ ነው የተዘገበው፡፡

ወደ አንፊልድ ለመሄድ ልቡ የሸፈተው ተጫዋቹ ከኒውካስል ዩናይትድ ጋር የገባበት ውዝግብ ክለቡ ከዝውውሩ ሊያገኝ የሚችለውን ዋጋ ሊያራክስበት እንደሚችል ተነግሯል፡፡

ከዚህ ቀደም እንደ አሌክሳንደር ኢሳክ ሁሉ ወደ ሌላ ክለብ ለመዘዋወር በመፈለጋቸው ምክንያት ከክለቦቻቸው ጋር ውዝግብ ውስጥ የገቡና ለቅጣት የተዳረጉ በርካታ ተጫዋቾች እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡

የወቅቱ የባሎንዶር እጩ ኦስማን ዴምቤሌ ከቦሩሺያ ዶርትመንድ ወደ ባርሴሎና ለማቅናት ሲል ከቡንደስሊጋው ክለብ ጋር ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ገብቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በፈረንጆቹ 2017 ኔይማርን በፒኤስጂ የተነጠቀው የካታላኑ ክለብ ፈረንሳዊውን የመስመር አጥቂ ለማስፈረም ያቀረቡት መነሻ የዝውውር ሂሳብ በዶርትመንድ ውድቅ መደረጉን ተከትሎ ተጫዋቹ ለክለቡ ሳያሳውቅ ከልምምድ በመቅረት አምጾ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ቦሩሺያ ዶርትመንድ ተጫዋቹን ደንብ በመተላለፍ ከስብስቡ ውጭ በማድረግ መቅጣቱም አይዘነጋም፡፡ በመጨረሻም ብቃቱ እየታየ የሚጨመር 42 ሚሊየን ዩሮን ጨምሮ በ147 ሚሊየን ዩሮ የዝውውር ሂሳብ መዳረሻው ካምፕ ኑ ሆኗል፡፡

መሰል ውዝግብ ውስጥ ገብተው ከነበሩ ተጫዋቾች መካከል ዌልሳዊው የቀድሞ የሪያል ማድሪድ እና ቶተንሃም ተጫዋች ጋሪዝ ቤል ይጠቀሳል፡፡

ተጫዋቹ በፈረንጆቹ 2013 በወቅቱ የተጫዋቾች ክብረ ወሰን በሆነ 100 ሚሊየን ዩሮ የዝውውር ሂሳብ ሪያል ማድሪድን ከመቀላቀሉ አስቀድሞ ከሰሜን ለንደኑ ክለብ ጋር እሰጣገባ ውስጥ ገብቶ እንደነበር ይነገራል፡፡

ጠንካራ ተደራዳሪ መሆናቸው የሚነገርላቸው የክለቡ ኃላፊ ዳንኤል ሌቪ ከተጫዋቹ ዝውውር ከፍ ያለ ገንዘብ ለማግኘት በማሰብ ሎስ ብላንኮዎቹ ያቀረቡትን የዝውውር ጥያቄ ውድቅ ማድረጋቸውን ተከትሎ ጋሪዝ ቤል መበሳጨቱ የሚታወስ ነው፡፡

ይህን ተከትሎ ተጫዋቹ በጉዳት በማሳበብ ከልምምድ መቅረቱን ተከትሎ ከስፐርስ የቅድመ ውድድር ዘመን ስብስብ ውጭ በመሆን ከክለቡ ጋር ውዝግብ ውስጥ መግባቱ ተገልጾ ነበር፡፡

በፈረንጆቹ 2021 ሀሪ ኬን ወደ ማንቼስተር ሲቲ ለማቅናት ከቶተንሃም ጋር የገባበት ውዝግብ የቅርብ ጊዜ ተውስታ ሲሆን፥ ዝውውሩ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ፒየር ኤሚሪክ ኦበሚያንግ ከቦሩሺያ ዶርትመንድ ወደ አርሰናል፣ ራሂም ስተርሊንግ ከሊቨርፑል ወደ ማንቼስተር ሲቲ፣ ፊሊፕ ኮቲኒሆ ከሊቨርፑል ወደ ባርሴሎና ከመዘዋወራቸው አስቀድሞ ከክለቦቻቸው ጋር ውዝግብ ውስጥ ከገቡ ተጫዋቾች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

አንፊልድን እያማተረ ያለው ስዊድናዊው የፊት መስመር ተጫዋች አሌክሳንደር ኢሳክ የተከተለው መንገድ ኒውካስል ዩናይትድን ማስቆጣቱ የተነገረ ሲሆን፥ ከሴንት ጀምስ ፓርክ የመኮብለሉ ነገር ግን የሚቀር አይመስልም፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.