Fana: At a Speed of Life!

ለምክክር ኮሚሽኑ ስራ ስኬት የአጋር አካላት ሚና ከፍተኛ ነው – መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ለምክክር ኮሚሽኑ ስራ ስኬት የአጋር አካላት ሚና ከፍተኛ ነው አሉ።

ኮሚሽኑ እስካሁን ባከናወናቸው ተግባራት የአጋር አካላት ሚናን የገመገመበትና በቀጣይ ለሚሠሩ ሥራዎች ግንኙነቱን የሚያጠናክርበት የውይይት መድረክ አካሂዷል።

መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) አጋር አካላት የወረዳ ተሳታፊዎችን ከመለየት ጀምሮ በአጠቃላይ ለኮሚሽኑ ስራ ስኬት ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው አንስተዋል።

በመድረኩ አጠቃላይ የኮሚሽኑን የስራ ክንውኖች የተመለከተ ገለፃ ያደረጉት ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር)÷ አጋር አካላት በቀሪ የኮሚሽኑ ተግባራት ትብብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

ከአጋር አካላት ጋር የሚደረግ ቋሚ የውይይት መድረክ አለመዘርጋትና የመረጃ ልውውጥ ስርዓት ወጥነት አለመኖር በውይይቱ ላይ እንደ ክፍተት ተነስተዋል።

በዚህም በቀጣይ ክፍተቶችን በማረም የተቀናጀ ስራ መስራት የሚያስችል ከኮሚሽኑና ከአጋር አካላት የተውጣጣ አስተባባሪ ቡድን ተቋቁሟል።

ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረሥላሴ ቡድኑ በቀጣይ ከትግራይ ክልልና ከዳያስፖራው ማህበረሰብ አጀንዳ ለማሰባሰብ በሚሰራው ስራ እና በዋናው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሂደት ላይ ከኮሚሽኑ ጋር በቅርበት እንዲሰራ ማስገንዘባቸውን የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።

በመድረኩ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፣ የእድሮች ጥምረት፣ የመምህራን ማህበር፣ ጀስቲስ ፎር ኦል፣ ደስትኒ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ ኢንክሉሲቭ ዲያሎግ እና የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን ተወካዮች ተሳትፈዋል።

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.