Fana: At a Speed of Life!

የቆቃ ግድብ በመሙላቱ ውሃ ይለቀቃል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በክረምት እየጣለ ባለው ዝናብ የቆቃ ግድብ ከመጠን በላይ በመሙላቱ ከነገ ጀምሮ ከግድቡ ውሃ ይለቀቃል አለ።

ግድቡን ለማስተንፈስ የሚለቀቀው ውሃ ከፍተኛ መጠን ያለው በመሆኑ በግድቡ ዙሪያ ያሉ ማህበረሰቦች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል።

በሚኒስቴሩ የገጸ ምድር ውሃ ዴስክ ኃላፊ ሚካኤል ብርሃኔ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ ውሃ የመያዝ አቅሙ 110 ነጥብ 3 ሜትር ከፍታ የሆነው የቆቃ ግድብ እስካሁን 109 ነጥብ 1 ሜትር ከፍታ ድረስ ውሃ ይዟል።

ስለሆነም ግድቡ ከአቅም በላይ በመሙላት ጉዳት ከማድረሱ በፊት ማስተንፈስ አስፈላጊ በመሆኑ ከነገ ጀምሮ ውሃ ይለቀቃል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ወንጂ ስኳር፣ መልካስ የምርምር ማዕከል፣ አፍሪካ ጁስ፣ የላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ፣ አዋሽ ወይነሪ እና መተሃራ ስኳር ፋብሪካ አካባቢዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም የአዋሽ ወንዝን የሚጋሩት አዳማ፣ መልካሳ፣ ቦሰት፣ ጀጁ እና መርቲ ወረዳዎች እንዲሁም የመካከለኛው አዋሽ አምቤራ እርሻ ልማት እና አሚባራ ወረዳ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ሚኒስቴሩ መልዕክቱን አስተላልፏል።

በአቤል ነዋይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.