ምን እያሉን ነው?
ከሁለት ሳምንት በፊት፤ ናይሮቢ የካምፓላ እንግዳዋን ከፍ ባለ ፕሮቶኮል ተቀበለች፡፡ ፍፁም አረንጓዴ አፀዱን በቀዩ ምንጣፍ ያደመቀው የናይሮቢ ስቴት ሃውስ መስተንግዶም በካምፓላ እንግዶች ዘንድ የተወደደ ሆነ፡፡
ከጥቅል ግቦች ውስጥ ንግድና ኢንቨስትመንትን ወደላቀ ምዕራፍ ለማሻገር ያለመው ይፋዊ ጉብኝት፤ ውይይቶችን አካሂዶና ስምምነቶችን ፈርሞ መቋጫውን የርዕሳነ ብሔሮቹ የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ አድርጓል፡፡
በሳቅ እና ጨዋታ ጭምር የታጀበው የዊሊያም ሩቶ እና ዩዌሪ ሙሴቬኒ የጋራ መግለጫ፤ ሳይታሰብ መራሩን ግን ደግሞ የማይቀረውን እውነት ይዞ ብቅ አለ፡፡
9ኛው የኡጋንዳ ፕሬዚዳንትና የ80 ዓመቱ ዩዌሪ ሙሴቬኒ ትዝብታቸውንና መብሰልሰላቸውን ያሳየና ነገሩን ለሚቃወሙትም የህሊና ሚዛን ተጠየቅን ያስከተለ ነጥብ አነሱ፡፡
“የባሕር በር ለሚለው እሳቤ እና ጥያቄ አመክንዮ የምንሰጥበት መንገድ ይገርመኛል፤ ደግሞም ያሳዝነኛል፤ እስኪ የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራትን ተመልክቱ! ቬትናም በሉ ቻይና ኢንዶኔዥያ ብትሉ ካምቦዶያ ትንሽም ይሁን ትልቅ ሀገር የባሕር በር እሳቤን ያለ አንዳች ኮሽታ ተግበረውት እየተመነደጉ ነው፡፡” ሲሉ የዓለምን እውነት አስታወሱ፡፡
ደግሞም ቀጠሉና “ዓለም ስምም ሆኖ የሚመራበትና የሚለማበት እሳቤ ብሎም ስርዓት ወደ አፍሪካ ሲመጣ ግን እጅና እግር እንዳይኖረው እናደርጋለን፡፡ ቀጣናችንን ተመልከቱ ኡጋንዳ ወደብ አልባ ናት፣ የደቡብ ሱዳን ዕጣ ፈንታም ይኸው ሆኗል፣ የሩዋንዳን አልነግራችሁም፣ ሌላው ቢቀር ኢትዮጵያ እንኳን እስካሁን የባሕር በር የላትም” ሲሉ ዕይታው በኢፍትሃዊነት የተጋረደውን የቀጣናው መንገድ ሃቅ ተጋፈጡ፡፡
“ሲጀምር አኅጉሩ በኢኮኖሚ የተሳሰረ አይደለም፡፡ ምክንያት የሚደረገውም የገበያ እጦት ነው፡፡ ወዳጄ አንደኛውን የኢኮኖሚ ውኅደት መፈጠሪያ መንገድ የባሕር በር ጥያቄን ፍታ፤ እንደመሪ እንደ ሚኒስትርነት ይሄን ጥያቄ ካልፈታን ወንበሩ ላይ ምን እንሰራለን?” ሲሉም ከዐለት የተስተካከለውን ጠንካራ ጥያቄ አነሱ፡፡
የፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ተጠየቃዊ ንግግር ወይ አልሰራን ለሚሰሩትም እንቅፋት ሆነናል ዓይነት ሆኖ ወደ ዙፋናቸው ሲመለሱ ለሚኒስትሮቻቸው ቀረበ፡፡ ዝምታ ሆነ፡፡ታሪክ ግን በልዩ መዝገብ አሰፈረው፡፡
ጥያቄው ግን ሉላዊ ነውና በካምፓላና ናይሮቢ ታጥሮ ሊቀመጥ አልቻለም፤ ይልቁንም ቱርክሜኒስታን ላይ ትልቁ አጀንዳ ሆነ፡፡ በዚያም የተባባሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጉዳዩን ከምድሪቱ ኢፍትሓዊ የንግድ ሥርዓት ጋር ሲያነፃፅሩት ተደመጡ፡፡
በቱርክሜኒስታን በተካሄደ 3ኛው የተባበሩት መንግሥታት በማደግ ላይ ያሉ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ጉባዔ ላይ ጉተሬዝ የሀገራቱ ጥያቄ አፋጣኝ መልስ የሚሻው ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የዓለምን 7 በመቶ ሕዝብ የሚያዋጡ እነዚህ ሀገራት በባሕር በር እጦት ሳቢያ ሉላዊ የንግድ ተሳትፏቸው አንድ ከመቶ ብቻ እንዲሆን ተፈርዶበታል ሲሉም ወቀሱ፡፡
ዋና ጸሐፊው ጉዳዩ ከሉላዊ ሁሉን ዐቀፍ የንግድ ስርዓት የተናጠበ የቅኝ ግዛት ዘመን ውርስ በመሆኑ ሀይ ሊባል ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
በመሆኑም ፍትሓዊ የንግድ ተጠቃሚነትን ለማንበር የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት የመልማት መብትና እድሎች ላይ ያለውን ገደብ ማንሳት ይኖርብናል፤ እንደ ተባባሩት መንግሥታትም ለዚህ ተፈፃሚነት እንሰራለን ሲሉ ንግግራቸውን ደመደሙ፡፡
አሁን ዙሩ ከሯል፤ ለፍትሓዊ ጥያቄው በጎ ምላሽ የመስጠትም፤ በድርቅና አቋም የመቀጠል ጉዞ እየተገለጠ ነው፡፡ እነሆ የብስራት ምላሼ ያላቸው ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ታንዛኒያ ውሳኔዋን አሳወቀች፡፡ “ባሕር በር አልባ ጎረቤቶቼ ሆይ ከእንግዲህ የዳሬ ሰላም ወደብን እንጋራለን”ም አለች፡፡
ወደቡን የማልማትና አቅም የማሳደግ ሥራ እየከወንኩ ነው ያለችው ታንዛኒያ በተለይም የኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ ከፍተኛ የመልማት ፍላጎት ወደቡን በጋራ ለመጠቀም እና በጋራ ለማደግ እንድትወስን እንዳስቻላት ይፋ አድርጋለች፡፡
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ እንደ አዲስ የተዘረጋው የምድሪቱ ስርዓት የወደብ እና የባሕር በርን ጉዳይ በልዩ ሁኔታ ቃኝቷል፡፡ ወዲህ ያለውን የላቀ ሁለንተናዊ ጠቀሜታ፤ ወዲያ ደግሞ ሊፈጥር የሚችለውን ቀውስ ቀድሞ በመተንበይ የሕግ ማዕቀፍ አበጅቶለታል፡፡
ለዚህም ውሃማ አካለቱን ወደብ፣ ባሕር በር፣ የባሕር መገናኛ፣ የባሕር ቦይ፣ ባሕረሰላጤ አሊያም ባሕረገብና የባሕር ወሽመጥ ሲል ለይቶ፣ ቅርፅ ሰጥቶ፣ አንቀጽ ጠቅሶ ዓለም አቀፍ ሕግ በሚል ዳጉሶ ሥራ ላይ አውሏል፡፡
ኢትዮጵያችን ከዓመት በፊት ከመሽኮርመም ዲፕሎማሲ ወጥታ ያነሳቸው የባሕር በር ጥያቄ እነዚህን ሕግጋት እና ሉላዊ አሰራሮች መሰረት ያደረገ ነው፤ ምንም አንኳ የኢትዮጵያን ዕድገት የማይሹ አካላት ሊያንሻፍፉት ቢሞክሩም ዛሬም አቋምና ፍላጎቷ እንዲዚያው ነው፡፡
እንደ ፈረንጆቹ የጊዜ ቀመር 1982 የወጣው ዓለም ዐቀፉ የባሕር ሕግ (United Nations Convention on the Law of the Sea- UNCLoS) የዓለም ሀገራት የባሕር ክልል እና ወሰንን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው መሰረታዊ መርሆዎችን አስቀምጧል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ 169 ሀገራት የፈረሙት ይህ ስምምነት 1994 ዓ.ም ወደ ስራ ሲገባ በመስኩ የተሻለ እና ገዥ ሕግ ለመሆን በቅቷል፡፡
በዚህ ሕግ በተለይም የባሕር በር ያላቸው ሀገራት መብትና ግዴታ በግልፅ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ከአንቀፅ 24 እስ 26 ያለው ከፍል የባሕር በር ያላቸው ሀገራት እንዳሻቸው የመሆንም ሆነ የማድረግ መብት እንደሌላቸው በግልፅ አስፍሯል፡፡
ዝርዝር የሕግ ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው የባሕር ክልላቸውን ለሰላማዊ እንቅስቀሴ እስከሆነ ድረስ ማሳወቅ፤ የባሕር ድንበራቸውን ነዳጅ ለመሙላት፣ ወደብና ትራንዚት ለፈለገ መርከብ ባለው ታሪፍ አገልግሎት የመስጠትን ግዴታ ሁሉ ያካተተ ነው፡፡
የባሕር በር ጉዳይን በተመለከተ የበለጠ የጠራው የህጉ ክፍል ደግሞ አንቀጽ 125 ነው፡፡ በተለይም ከተራ ቁጥር አንድ እስከ ሦስት ያለው ክፍል፡ ባሕር በር አልባ አገራት፡ ባላቸው ሀገራት በኩል በማንኛውም አይነት መጓጓዣ መንገድ፡ ከባህር ጋር የሚገናኙበት ነጻነት አላቸው ሲል አስፍሯል፡፡ እንዴት ለሚለው ደግሞ ፤የባሕር በር ካለው ሀገር ጋር በሚደርግ ድርድርና ስምምነት ይከወን ይላል፡፡
ዘርዘር ያሉ ግዴታዎችን በባለወደብ ሀገሮች ላይ የሚጥለው ህጉ ማሰሪያውን እንዲህ አስፍሯል፤ የባሕር በር ያላቸው አገሮች የባሕር በር የሌላቸው አገሮችን ህልውናና ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥል እንቅስቃሴ ከማድረግ መቆጠብ ይኖርባቸዋል በማለት፡፡
የዚህ ጽሑፍ ከታቢ ይህን ሐሳብ መቋጫ ያደርጋል፡- አይደለም ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ መብት ኖሮ ቀርቶ፣ ሀገራት ሉላዊ በሆነው አሰራር እና ሕግጋት ብሎም በተራማጅ እሳቤ ጭምር የኢትዮጵያችን አብሮ የመልማትና የማደግ ጤነኛ ትልም መሬት መንካቱ አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ ሕግ እና የሥርዓተ ማኅበሩ አሰራር ምክንያት ስሪታቸውም ሆነ ስርዓታቸው ወደብ አልባ የሆኑ ሀገራት የባሕር በር ተጠቃሚ ሲሆኑ ምድሪቱ ምስክር ሆኖለችና!
ባለፉት ሁለት ሳምንታት ያየናቸው የባሕር በር (access to the sea) ጥያቄ ያገኘው ትኩርት ብሎም የተስተዋሉ ጅምር በጎ ምላሾች የታላቂቷን ኢትዮጵያ ቀጣይ መዳረሻ ጠቋሚ ሆነውም የሚወሰዱ ናቸው፡፡
በአስማረ ቸኮል
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook WMCC
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!