የቶዮ ጸሐይ ኃይል ማመንጫ ፋብሪካ ለወጪ ንግድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገኘው የቶዮ የጸሐይ ብርሐን ኃይል ማመንጫ ፋብሪካ ለማኑፋክቸሪንግ ወጪ ንግድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገኘውን የቶዮ የጸሐይ ብርሐን ኃይል ማመንጫ ፋብሪካ የሥራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቬይትናም የቶዮ ጸሐይ ኃይል ማመንጫ ፋብሪካ በነበራቸው ጉብኝት ከኩባንያው ፕሬዚዳንት ጋር የጸሐይ ብርሃን ኃይል ማመንጫዎችን በኢትዮጵያ ለማምረት ተስማምተው እንደነበር አስታውሰዋል።
በዛሬው ዕለትም ኩባንያው በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከጸሐይ ብርሃን ኃይል ማመንጫዎችን እያመረተ እንደሚገኝ በመመልከታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
ማምረቻው በከፍተኛ ጥራት ከፍተኛ ምርት የማምረት አቅም የተላበሰና በዘመናዊ የማሽን ሥርዓት የሚሰራ መሆኑን ጠቁመው ፥ የምርት ውጤቱ ለማኑፋክቸሪንግ ወጪ ንግድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል ነው ያሉት።
ሁለት ተጨማሪ ማምረቻዎች በግንባታ ሒደት ላይ የሚገኙ ሲሆን÷ ወደ ምርት የገባውን ማምረቻ ሥራ ሒደት መመልከታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
ይህ ሥራ እሴት የተጨመረባቸውና ያስቀመጥናቸውን ግቦች እንዲሁም ፖሊሲዎች የሚያሳኩ ጨዋታ ቀያሪ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ከሚያደርገው የኢንቨስትመንት ስትራቴጂ ጋር የተጣጣመ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡