Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ለዜጎች ተጠቃሚነት በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ ተደርሷል – ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ12ኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ ተደርሷል አሉ የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፡፡

“ከፖለቲካ እስከ ብልፅግና” በሚል መሪ ሀሳብ በጋና አክራ የተካሄደው ጉባዔ የዜጎችን ሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር ብለዋል።

መድረኩ ለአህጉራዊ ለውጥ፣ ለዜጎች ተጠቃሚነትና ለሀገረ መንግሥት ግንባታ በትብብር ለመስራት መግባባት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት።

በጉባኤው በአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ትብብርን ለማጠናከርና ለአህጉራዊ እድገት ተስፋ የሚሆን የፓርቲዎች ጥምረትን እውን ለማድረግ ያለመ ውይይት መካሄዱንም ተናግረዋል።

ፓርቲዎች ኢኮኖሚያዊ ሽግግርን፣ የዘላቂ ሰላም ግንባታ እና የሀገረ መንግስት ግንባታን ለማረጋገጥ በትኩረት መስራት እንዳለባቸውም መነሳቱን ገልጸው፤ ይህም ጠንካራ አፍሪካን ለመገንባት ትልቅ መሠረት ይጥላል ብለዋል።

የአፍሪካ ፖለቲካን ካለመተማመንና ከጥርጣሬ አካሄድ በማውጣት በጋራ አህጉራዊ አጀንዳዎች ላይ አሻራን ለማኖር የሚያስችል ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።

በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፤ ፓርቲዎች ለሁለንተናዊ ዕድገት ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው በመግለጽ በመተማመን፣ መተባባር እና ለጋራ ዓላማ መግባባት ፈጥረው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው መናገራቸውንም አንስተዋል።

ፓርቲዎች ለጠንካራ ሀገርና አህጉር ግንባታ፣ ለሀገረ መንግስት ቅቡልነትና ለተረጋጋና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህል ግንባታ ትልቅ ትኩረት በመስጠት መስራት እንደሚገባ መግባባት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል።

ፓርቲዎች ውስጣዊ ሪፎርም በማድረግ ለአዎንታዊ እና ዘላቂ ሰላምን ግንባታ አሻራቸውን ማኖር እንዳለባቸውም መግባባት ላይ እንደተደረሰ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.