ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በአርቲስት ደበበ እሸቱ ሕልፈት የተሰማቸውን ሃዘን ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በአርቲስት ደበበ እሸቱ ሕልፈት የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት የሃዘን መግለጫ÷በስራው ሁሉ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን እንደወገነ በኖረው የሀገራችን የኪነጥበብ አድባር ደበበ እሸቱ ሕልፈት የተሰማኝ ሃዘን ጥልቅ ነው ብለዋል።
የእርሱ ውግንና ሁሌም ለኢትዮጵያ ሆኖ ለመዝለቁ በዘመኑ ሁሉ የሰራቸው የጥበብ አሻራዎቹ የተግባሩ ህያው ምስክሮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
አርቲስት ደበበ ከወጣትነት እስከ ሕልፈቱ ለኢትዮጵያና ለኪነጥበብ የተጋ፣ ከሥራው ሞት የለየው ብርቱ ሰው ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ለአርቲስቱ ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶች፣ አድናቂዎች እና ለኪነ ጥበቡ ማሕበረሰብ መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡