Fana: At a Speed of Life!

አርቲስት ደበበ እሸቱ ለሀገሩ ያለው ፍቅርና አቋም የጸና፣ በየጊዜው የማይለዋወጥ ታላቅ የጥበብ ሰው ነው – ነብዩ ባዬ (ረ/ፕ)

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አርቲስት ደበበ እሸቱ ለሀገሩ ያለው ፍቅርና አቋም የጸና፣ በየጊዜው የማይለዋወጥ እና በኃያል ክህሎቱ ጥበብን ለዓለም መግለጥ የቻለ ታላቅ ሰው ነው አሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴዔታ ነብዩ ባዬ (ረ/ፕ) ፡፡

ሚኒስትር ዴዔታው በአርቲስት ደበበ እሸቱ ሕልፈት የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል።

በዚህም አርቲስት ደበበ እሸቱ ከልጅነቱ ጊዜ ጀምሮ በጥበብ ዓለም በተዋናይነት፣ በደራሲነት እና በአዘጋጅነት በመስራት ዘመን የማይሽረው አሻራ ማኖሩን ተናግረዋል፡፡

አንጋፋው ከያኒ በኢትዮጵያ የጥበብ መድረክ ብዙ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመው÷ በኪነ ጥበብ ሥራዎቹም ሀገሩን በጉልህ ያስጠራና እና ያስተዋወቀ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

ወደ ውጭ ሀገር ሄደው ተምረው ወደ ሀገራቸው በመምጣት አገልግሎት ውስጥ ከገቡት በቀዳሚነት ስሙ የሚጠራ አርቲስት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህም ከወዳጁ አርቲስት ወጋየሁ ንጋቱ ጋር በመሆን በብሔራዊ ቴአትር ሰፊ የጥበብ አስተዋጽኦ ያበረከተ መሆኑን ጠቁመዋል።

አርቲስት ደበበ እሸቱ ከተጫወታቸው ተውኔት መካከልም እናት ዓለም ጠኑ፣ ያለአቻ ጋብቻ፣ ጠልፎ በኪሴን ጨምሮ የመንግስቱ ለማን እና የጸጋዬ ገብረ መድህን ታላላቅ የተውኔት ስራዎች ላይ መጫወቱን ተናግረዋል፡፡

አርቲስት ደበበ እሸቱ በቬኑሱ ነጋዴ እና ንጉስ ሊር ከተወነባቸው የትርጉም ተውኔት መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቁመው÷ በሀገር ውስጥ ብቻም ሳይሆን ከሀገር ውጭም በኪነ ጥበብ ስራዎች ላይ ተሳትፏል፡፡

በመላው ዓለም የኢትዮጵያን ጥበብ፣ ኃይል፣ ተሰጥኦ፣ ባህል፣ ታሪክ ምልክቶችን የሚገልጡ ሥራዎችን መስራቱን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም ሆሊውድ ውስጥ ‘ሻፍት ኢን አፍሪካ’ የሚል ፊልምን ጨምሮ በሌሎችም ላይ መሳተፉን ጠቅሰው÷ በአፍሪካ ደረጃ የተዋንያን ማህበር በማቋቋም በመስራች ፕሬዚዳንትነት ጭምር የመራ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

አርቲስት ደበበ እሸቱ የመብት ተሟጋች እንደነበር አስታውሰው÷ከያኒያን ሀገራቸውን መውደድ፣ ለሷም መስራት እንዳለባቸው እንዲሁም ለሀገር መቆምን በተግባር ያስተማረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አርቲስት ደበበ የዘመን መለዋወጥ የማይበግረው፣ ለሀገሩ ያለው ፍቅርና አቋም የጸና መሆኑን አውስተው÷ጥልቅ የሆነ የሀገር ፍቅሩ ለወጣቶችም አርዓያ መሆን የቻለ ታላቅ የጥበብ ሰው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.