በአዲስ አበባ የሚካሄዱ ጉባኤዎችን ለአረንጓዴ ዲፕሎማሲ መጠቀም ይገባል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ የሚካሄዱ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ለአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ስራ መጠቀም ይገባል አሉ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን፡፡
የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ምሁሩ ብሩክ ኃይሉ (ፕ/ር)፥ ኢትዮጵያ ከሳምንታት በኋላ የምታስተናግደው 2ኛው የአፍሪካ የአከባቢ ጥበቃ ጉባኤ የአረንጓዴ አሻራ ተሞክሮዎቿን የምታካፍልበት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርና በአፈርና ውሃ ጥበቃ የተከናወኑ ተግባራት ጉባኤውን ለማስተናገድ ተማራጭ እንዳደረጋት ጠቅሰው፥ ሁነቱ ተጽእኖ ፈጣሪነቷን የሚያጎላ ነው ብለዋል፡፡
ሌላኛው የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ምሁር ጥላሁን ሊበን በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ ያከናወነቻቸውን ተግባራት በማካፈል ጉባኤውን ለአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ስራ መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ጉባኤው ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ የሰራቻቸውን ስራዎች ለዓለም የምታሳይበት እንደሚሆን ነው ምሁራኑ የገለጹት፡፡
በመቅደስ ከበደ