በአማራ ክልል የወባ ሥርጭትን ለመከላከል…
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የወባ በሽታ ሥርጭትን ለመከላከል በቅንጅት እየተሰራ ነው አለ የክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፡፡
በኢንስቲትዩቱ የወባ ፕሮግራም ባለሙያ አቶ ይርዳው እምሩ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ በክልሉ የወባ በሽታ ሥርጭት በስፋት የሚስተዋልባቸው ወረዳዎች ተለይተዋል፡፡
በእነዚህ ወረዳዎች ያለውን የወባ ሥርጭት ለመቆጣጠርም ግብረ ሃይል ተቋቁሞ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት፡፡
በዚህ መሰረትም የወባ መከላከያ አጎበር ሥርጭት እና የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በክልሉ 878 ሺህ በላይ አጎበር ለማሰራጨት ታቀዶ አሁን ላይ በመጀመሪያ ዙር 390 ሺህ አጎበር መሰራጨቱን አመልክተዋል፡፡
በሌላ በኩል በ40 ወረዳዎች 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ቤቶች ላይ የኬሚካል ርጭት ለማከናወን ታቀዶ የነበረ ቢሆንም ለክልሉ የደረሰው ኬሚካል ግን ለ14 ወረዳዎች ብቻ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡
በዚህም 500 ሺህ በላይ የሚሆኑ ቤቶችን በጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት ተደራሽ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
ለማሰራጨት የታቀደው አጎበር እና ኬሚካል ክልሉ በወቅቱ ባለማግኘቱ የወባ በሽታ መከላከል ሒደቱን አስቸጋሪ እንዳደረገው አብራርተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በክልሉ ያለው የወባ ሥርጭት በሚጠበቀው ልክ አለመቀነሱን ጠቁመው÷ ሥርጭቱን ለመቆጣጠር የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ሕብረተሰቡም አጎበርን በአግባቡ በመጠቀም፣ ለወባ መራቢያ የሆኑ አካባቢዎችን በማጽዳትና ሕመም ሲሰማው በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ጤንነቱን እንዲጠብቅ አስገንዝበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ