Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል የደመወዝ ማሻሻያውን ተከትሎ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል የደመወዝ ማሻሻያውን ተከትሎ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት ቁጥጥር እየተደረገ ነው አለ የክልሉ ንግድ ቢሮ፡፡

የቢሮው ም/ሃላፊ አቶ ተስፋዬ ገሾ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ በክልሉ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች እጥረት እንዳይከሰት በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡

ከደመወዝ ማሻሻያው ጋር ተያይዞ ነጋዴዎች ያለአግባብ ዋጋ እንዳይጨምሩ ቁጥጥር የሚያደርግ አቢይ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል፡፡

የምርት አቅርቦትን ለማሳለጥም ኮሚቴው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ነው ያስረዱት፡፡

በዚህም ምርቶች በእሑድ ገበያዎች እና በገበያ ማዕከላት በበቂ ሁኔታና በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕብረተሰቡ እንዲያቀርቡ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በገበያ ቦታዎቹ የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶች አቅርቦትን ለማጠናከር የገበያ ትስስር መፍጠር ላይ እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡

በሌላ በኩል ምርትን በመደበቅና በማከማቸት የገበያ ዋጋ አለመረጋጋት ለመፍጠር የሚሰሩ ነጋዴዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ ጠቁዋመል፡፡

የደመወዝ ማሻሻያውን ተከትሎ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት፡፡

ሕብረተሰቡ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉና ምርቶችን የሚያከማቹ ነጋዴዎችን ሲመለከት ጥቆማ እንዲሰጥም አቶ ተስፋዬ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

መንግስት ከመጪው መስከረም 2018 ጀምሮ ለመንግስት ሠራተኛው ተጨማሪ የደመወዝ ማሻሻያ ለማድረግ መወሰኑ ይታወቃል፡፡

ለዚህም ተጨማሪ 160 ቢሊየን ብር በጀት የተመደበ ሲሆን ÷ ሠራተኛው ሥራውን በውጤታማነት በመፈፀም ለሀገራዊ ዕድገት የድርሻውን መወጣት ይጠበቅበታል።

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.