Fana: At a Speed of Life!

ለቀጣይ ፕሮጀክቶች ዕውቀትና ልምድ ያሸጋገረው ሕዳሴ ግድብ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ተወዳዳሪ ባለሙያዎች የተፈጠሩበት እና በቀጣይ ለሚሰሩ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ዕውቀት እና ልምድ የተሸጋገረበት ነው አሉ ምሁራን።

ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ የነበራቸው ምሁራን እንዳሉት፤ ግድቡ ኢንዱስትሪዎችን እና መሠረት ልማቶችን ለማስፋፋት የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የሲቪል ምህንድስና ትምህርት ክፍል ኃላፊና መምህር በረከት ነፃነት እንዳሉት፤ የግድቡ ግንባታ ሂደት የዘርፉ ባለሙያዎችና ኮንትራክተሮች ትልቅ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርጉ አስችሏል።

በተለይም ኮንክሪት በፍጥነት፣ በጥራትና በብዛት ተመርቶ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ መዋሉ ለቀጣይ መሰል ፕሮጀክቶች ትምህርት ሰጥቷል ብለዋል።

በተጨማሪም ግድቡ ከፍተኛ የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራዎች ያሉት መሆኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንድንጠቀም፣ እንድናስተዳድር እና ቴክኖሎጂን አላምደን በሀገር ውስጥ መተካት የሚያስችል ዕድል ፈጥሯል ነው ያሉት።

በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሳይንቲፊክ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ሙሉነህ ለማ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የግድቡ ኤሌክትሮ መካኒካል ሥራዎች በቴክኖሎጂ የታገዘና ውስብስብ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ከጥራት እስከ ገጠማ ያሉ ሁነቶች ለኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ከፍተኛ ልምድና ክህሎት ያስገኘ ነው ብለዋል።

ምሁራኑ በግድቡ የሲቪል እና ኤሌክትሮ ሜካኒካል ግንባታ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን ባገኙት ዕውቀትና ልምድ በራስ መተማመናቸው እንደጨመሩ ጠቁመዋል።

ግድቡ የውሃ ሃብትን የመጠበቅ እና የመጠቀም ዓቅምን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ገልጸው፤ ወንዞችን ለኃይል ማመንጫ እና ለመስኖ የሚያውሉ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ለመስራት የሚያስችል እውቀት፣ ልምድና የቴክኖሎጂ ሽግግር ተደርጎበታል ብለዋል፡፡

በአስጨናቂ ጉዱ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.