Fana: At a Speed of Life!

ለህገ ወጥ ስደት መከራ ከመዳረግ በፊት . . .

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሁለት የተለያዩ ህገ ወጥ ጉዞዎች የባከኑ ስድስት አመታት፣ እንግልት እና ስቃይ ያጀቧቸው ጊዜያት የባለታሪካችን የሕይወት ደርዝ ሆነው አልፈዋል፡፡

በ22 ዓመት እድሜዋ ያማተረችው የስደት ሕይወት በወጉ ጡት ያልጠባች አራስ ልጇን ለትዳር አጋሯ ትታ የፈተና መንገድ እድትጓዝ አስገድዷታል፡፡

ከፋና ዲጂታል ጋር ቆይታ ያደረገችው ባለታሪካችን የኔነሽ ጥላሁን፤ ወደ ቤይሩት ለመሰደድ አስባ የጀመረችው የህገ ወጥ ጉዞ ሱዳን ስትደርስ መከራ እንድትጋፈጥ አድርጓታል፡፡

በሱዳን ያሳለፈቻቸው ሰባት ቀናት ክፉኛ የተጨነቀችባቸው ብሎም ተስፋ የቆረጠችባቸው ነበሩ፡፡

ሕይወቷን ለመቀየር ተስፋ ያደረገችበት መዳረሻዋ ቤይሩት በሰማችው እና ባሰበችው ልክ መሆኑ ቀርቶ በተቃራኒው ሆኖ የከፋ ችግር ውስጥ መግባቷን አስገነዘባት።

ውጣ ውረድ እና ስቃይ እስኪበቃኝ አይቻለሁ የምትለው የኔነሽ፤ ግፉ ቢበዛባት፣ ስቃዩ ቢበረታባት ወደ ሀገሯ መመለስ አማራጭ ሆኖ በማግኘቷ ለመመለስ ወሰነች።

መገፋት፣ በሰው ሀገር መሰቃየት እና ያሰቡትን አለማግኘት ከመጀመሪያ ስደቷ ያስተናገደቻቸው እውነቶች ናቸው፡፡

ይህንን አስከፊ የስደት ምዕራፍ ብትዘጋውም በቀጣዩ የህገ ወጥ ስደት ምዕራፍ ውስጥ ገብታ ሌላ የመከራ ጽዋን ተጎንጭታለች።

በሁለተኛ የህገ ወጥ ስደት መዳረሻዋ ግብፅ ያስተናገደችው ችግር ከመጀመሪያ የስደት የባሰ ሆኖ ጠበቃት።

ይህ የስደት ምዕራፍ አዕምሮዋ ከሚችለው ስቃይና መከራ ተሻግሮ በምን ምክንያት እንደሆነ ሳታውቅ ለአዕምሮ ጤና ችግር አጋለጣት።

ጠያቂ በሌለበት አይዞሽ ባይና አጋዥ በማይገኝበት የስደት ህይወት ላይ ይህንን ህመም ማስተናገዷ ነገሮችን እንዳከበደባት እንዲሁም ልጆቼን አገኝ ይሆን በሚል አብዝታ ስትጨነቅ መቆየቷን ትናገራለች፡፡

እንደ አወጣጧ ሁሉ አገባቧም ህገ ወጡን መንገድ የተከተለ መሆኑ ከእርሷ ባለፈ በርካቶች ሲሰቃዩና በረሃ ሲበላቸው የተመለከተችው የኔነሽ፤ እኛ በብዙ ልፋት እና ድካም ወደ ሀገር ስንገባ፤ በዛው መጠን ህገ ወጥ በሆነ መልኩ ለመውጣት መንገድ የሚወጡ ብዙ ናቸው ትላለች፡፡

ይህ ሁኔታ ደግሞ የቀመሰችውን የስደት ፈተና የሀገሯ ልጆች እንዳያገኛቸው የምትችለውን ሁሉ ለማድረግ እንድትነሳ አድርጓታል።

በዚህም ከአራት አመት በፊት ‘ካስማ የበጎ አድራጎት ድርጅት’ን እንደ እሷ በመሰል የስደት ጉዞ ችግር እና ስቃይ ካስተናገዱ 14 የስደት ተመላሾች ጋር በመሆን አቋቋመች።

ለማርዳትም ሆነ ለማውጋት በአካል እንደተገኘ ሰው እማኝ የለም የምትለው የካስማ መስራቿ፤ ድርጅቱ በስደት ፈተና ኢትዮጵያውያን እንዳያልፉ ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ እየሰራ ነው ብላለች።

ለስደት የሚነሱት በመረጃ የተመሰረተ ጉዞ እንዲያደርጉ፤ የሚመለሱትን ደግሞ አሰልጥኖ፣ አስተምሮ ከህብረተሰቡ ጋር ማቀላቀል የድርጅታቸው አላማ መሆኑን ገልጻ፤ ባለፉት 2 አመታት ከ300 በላይ ሴቶችን በማሰልጠን በሀገር ውስጥ በተለያዩ የስራ ዘርፎች እንዲሰማሩ አድርገናል ስትል ገልጻለች።

ብዙዎች ውጪ ናፋቂ ሳይሆኑ በሀገር ውስጥ ያሉ የስራ አማራጮችን እንዲያዩ እመለክራሉ የምትለው የኔነሽ፤ ስደትን ብቻ አማራጭ ከማድረግ ግራ ቀኙን መመልከት ይገባል ትላለች፡፡

መሄድ የግድ ከሆነም መንግስት ያደረጋቸው የውጪ ሀገር የስራ ስምሪት ስምምነቶች ላይ የተመሰረተ ጉዞ መሆን እንዳለበት አስገንዝባለች።

መረጃ ኖሯቸው፣ ስልጠና ወስደው እንዲሁም መዳረሻቸውን እና የመመለሻ ጊዜ አውቀው ሊጓዙ ይገባል ብላለች።

በኤርሚያስ ቦጋለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.