የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በሁለት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ዛሬ ባካሄደው 5ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ስብሰባ በቀረቡ ሁለት አጀንዳዎች ላይ ውይይት በማድረግ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
በመጀመሪያ አጀንዳው በኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ውስጥ በመንግስትና የግል አጋርነት በተፈረመው ስምምነት መሰረት ለሚለሙ 30 ፕሮጀክቶች ከ733 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ 37 አልሚዎችን ለመደገፍ በቀረበው አጀንዳ ላይ ተወያይቷል፡፡
በዚህም ፕሮጀክቶች ካላቸው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ፣ ከሚፈጥሩት ሰፊ የስራ ዕድል እና የከተማ ልማት አንፃር በመገምገም ካቢኔው በቀረበ የውሳኔ ሀሳብ ላይ ተወያይቶ ውሳኔውን አፅድቋል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የአሰልጣኞች የዝውውርና የምደባ አፈፃፀም ደንብ በተመለከተ ውይይት አድርጓል።
በውይይቱም በቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት ጥራት ያለው ሥልጠና ለመስጠት፣ ኮሌጆችን ውጤታማ ከማድረግ እና በተደራጀ አግባብ ለመምራት በሚያስችል መልኩ የደንቡ መውጣት እገዛው የጎላ በመሆኑ የምደባ ደንቡ እንዲፀድቅ መወሰኑን የአስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።