በመዲናዋ ለአገልግሎት ጉቦ የጠየቁ አመራሮች በቁጥጥር ሥር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የቄራዎች ድርጅት የሚሰጠውን አገልግሎት ለማግኘት የሄዱ ተገልጋዮችን ገንዘብ የጠየቁ ሁለት ተጠርጣሪ አመራሮች በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰይድ እንድሪስ ከማል እና ምክትላቸው አቶ የሱፍ ድሪብሳ ማሞ ናቸው፡፡
አመራሮቹ ገንዘብ ካላመጣችሁ አገልግሎት አታገኙም በሚል እንግልት ሲፈጠሩ ቆይተው በደረሰ ጥቆማ ዛሬ ከተገልጋይ ጉቦ ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ ተይዘው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የከንቲባ ጽ/ቤት ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡
ሕብረተሰቡ በቀጣይ ሙስናን ለመከላከል በሚደረገው ትግል ከከተማ አስተዳደሩ ጎን በመሆን በቅንጅት እንዲሰራ ጥሪ ቀርቧል፡፡
ነዋሪዎች መሰል የሙስና ተግባራትን ሲመለከቱም ለከንቲባ ጽ/ቤት የሙስና ወንጀል ጥቆማ ተቀባይ በመጠቆም ሙስናን የመከላከል ሚናቸውን እንዲወጡም ተጠይቋል፡፡