ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ለውጥ ያስመዘገበችበት የአረንጓዴ ኢኮኖሚ …
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መቀነስ የሚያስችል የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ገቢራዊ በማድረግ ሁሉን አቀፍ ለውጥ አስመዝግባለች አለ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በፓን አፍሪካ የአየር ንብረት ፍትሕ ጥምረት የተዘጋጀው 5ኛው የ2025 የአየር ንብረት ፍትሕ የናይሮቢ የክረምት ትምህርት መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ የናይሮቢ የአየር ንብረት ለውጥ የክረምት ትምህርትን ማዘጋጀቷ ታላቅ ኩራት ነው።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ የተለያዩ የፖሊሲ ርምጃዎችን በወሰደችበትና 2ኛውን የአየር ንብረት ጉባዔ በምታስተናግድበት ወቅት በመሆኑ ክብር ይሰማናል ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ ከ141 የዓለም ሀገራት የተወጣጡ የአየር ንብረት ለውጥ ወጣት መሪዎች እንደታደሙ ጠቅሰው÷ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል ሚናቸው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ በየዓመቱ ከ2 እስከ 5 በመቶ ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት እንደሚያሳጣ የተናገሩት ሚኒስትሯ ÷ ይህም በአፍሪካ ጉዳቱ የከፋ መሆኑን ያሳያል ነው ያሉት፡፡
አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ከአራት በመቶ የማይበልጥ ዝቅተኛ አስተዋፅኦ ቢኖራትም የጎላ ጉዳት እንደምታስተናግድ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የዓለም የአየር ንብረት ፋይናንስ ሥርዓት ለማስተካከል ለአፍሪካውያን ትብብር፣ ቁርጠኝነት፣ ፍትሐዊነት እና ተፈጥሮን መሰረት ያደረገ መፍትሄ ወሳኝ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽዕኖ በዘላቂነት ለመፍታት አፍሪካውያን አፍሪካዊ መፍትሔ መፈለግ እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ሥርዓት ተፈጥሮን መሰረት ያደረገ ርምጃ በመውሰድ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቧን ጠቁመው ÷ የአየርን ንብረት ለውጥን ከፓሪስ ስምምነት ቀድማ ርምጃ መውሰድ መጀመሯን ተናግረዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጭነት በተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን እንዲሁም በአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ 50 ሚሊየን ሄክታር የተራቆተ መሬት መመለስ መቻሉን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ 96 በመቶ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከታዳሽ ኃይል እንደምታመነጭና ውጤቱ የሃይል ሽግግር ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ አዲስ አበባን ጨምሮ ከ60 በላይ ከተሞችን በኮሪደር ልማት ምቹና አረንጓዴ እያደረገች መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
የወንዝ ዳርቻ ልማቶች የኢትዮጵያን መልክ የሚገልጹ፣ የተፈጥሮ ሚዛንን የሚጠብቁ፣ ውብ ከባቢን የሚፈጥሩ ሰው ተኮር ሥራዎች መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከውጭ ስንዴ በማስገባት የምትታወቅበትን ዘመን ታሪክ በማድረግ ተጨባጭ ውጤት ማስዝገቧንም ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል፡፡
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!