ከአባይ ወደ ዓባይ
ካይረባ ጓደኛ ይሻለኛል ዓባይ…ይሻላል ተከዜ፣
በዜት እንሻገር ………. ያሰኛል ሁል ጊዜ፡፡
ሊቀመኳስ ቻላቸው አሸናፊ
የሱዳኗ መናገሻ ካርቱም ከታላቋ ኢትዮጵያ ጥቁር እንግዳ ይመጣል ተብላ ሽር ጉድ ላይ ነች፡፡
በርግጥም ሺሕ ዓመታትን ዋስ የሚጠራ ታሪክ እና ሥልጣኔን የከተበ፣ ጥልቅ እና መልከ ብዙ የባሕል እሴትን የቀመረ፣ እኛነትን በተግባር ሰንደቁ ያደረገ፣ አይደለም ተጽፎ ተነገሮ የማያልቅ ኢትዮጵያዊነትን በኪን ያዋዘ የከያኒዎች ቡድን ከአዲስ አበባ ወደ ካርቱም አምርቷል፡፡
ካርቱም የምንጊዜም አቀንቃኟ ሙሐመድ ወርዲ እንደተኮላተፈው ሁሉ የኪን አምባሳደሮችን ጤና ይስጥልኝ! እንደምን ናችሁ? ስትል በአማርኛ የጎረቤት ወጉን፣ የእንግዳ ማዕረጉን አደረሰች፡፡
ልዑኩ ከካርቱም ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ሆቴል ጉዞ ሲጀምር ግን ያልተጠበቀው ሆነ ፤ የልብ ምትን ቀጥ የሚያደርግ ድብልቅልቅ ያለ የስሜት ክስተት!
ልኬት ለሌለው ንዴትና ብስጭት የሚዳርግ፣ ቁጭቱም፣ ፀፀቱም፣ ናፍቆቱም እንደ እናት ሞት መቼም የማይችሉትናየማይረሱት፣ተፈጥሮን በፍትሕ ዓይን የሚሞግት አይነት ፍፁም እንግዳ ስሜት ኢትዮጵያዊያኑ ላይ ተፈጠረ፡፡
ይህ መልከ ብዙው ስሜት ለጸሐፌ ተውኔት ጌትነት አንየው ደግሞ የተለየ ሆነ፡፡
በመንገዳቸው ካርቱምን ለሁለት ሰንጥቆ የሚያልፈውና ድብልቅልቁን ስሜት የፈጠረው የእኛው አብራክ ሩቅ ተጓዡ የዓባይ ወንዝ ነበር ፡፡
ቅፅበቱ ለዓመታት ከዓይንና ጆሮ የተሰወረን የእናት ልጅ በውጭ ሀገር ሲንከራተት እንደማግኘት ዓይነት፤ የእኔ ያሉት ሰው ከራሱ ሰው እየቀማ ለባዕድ ሲያድር እንደሚፈጠር የመብገን ስሜት! ነበር ፡፡
ያ ለያዥ ለገናዥ ያስቸገረው ባለ ብርቱ ኃይሉ ዓባይ፤ ከዶንዶር ወንዝ መክሮ፣ ከበለስ ሽርክ ሆኖ፣ ከዴዴሳ ጋር አብሮ ፣ ጀማ ወንዝን አሸፍቶ፣ መገጭን ጉማራን አሳድሞ ሲጣደፍ…ሲቸኩል በቤቱ ቤተኛ ለመሆን አሻፈረኝ ሲል እንዳልታየ ካርቱም ውስጥ ስሙንም ግብሩንም ቀይሮ ሲብሰከሰክ ተገኘ፡፡
በርግጥም የእኛው ዓባይ ስሙን ናይል ብሎ፣ ያን ቁጣ ፍጥነቱን በስክነት ተክቶ፣ ድፍርስ መልኩን ሰማይ አስመስሎ፣ ከእብሪቱ ለመጉደል የታኅሣሥ ቀጠሮ የሚያስይዘው ዓባይ የጀልባ መፈንጫ ሆኖ፣ ጭራሽ የአስፋልት ማጠቢያ ተደርጎ በራሱ ልጆች፤ በዘመዶቹ ዐይን መታየቱ ከአዕምሮም በላይ ነበር፡፡
ይህ በተባ ብዕሩ የኢትዮጵያን ዝማኔ “የቴዎድሮስ ራዕይ” ሲል ላስተዘተ፣ ጀግንነትን “በአሉላ አባ ነጋ” መስሎ ሳይሆን ሆኖ ላሳየ፣ የበላይ ዘለቀን ድንበር አልባ ዓርበኝነት “በአባ ኮስትር” ቴአትር ኅያው ታሪክ ለዘከረ፣ የባሕል ወረራን “ቅኔ ነን ሀበሾች”ን ተቀኝቶ ለመከተ፣ የሕንደኬው እና የእቴጌ ጣይቱ ጥንቁቅ አዘጋጅ፣ የመንፈስ ከፍታ ለሰበከው! አዎን ለእርሱ ለጌትነት እንየው ዓባይ ካርቱም ውስጥ ሲታይ በቁጭት ወላፈን የሚጋረፍ ነበር ፡፡
13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ዓባይን የመገደብ የነ አፄ ዳዊት የሐሳብ ውጥን፣ የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መሰረት ድንጋይ ጅማሮ ዳር አለመድረሱ እንኳንስ ለዜጋው ሚዛን ዕይታ ላለው ባዕድም እንደ እግር እሳት የሚያንገበግብ ነበር ፡፡
ሆኖም ታሪክን በቅጡ መከወን ደግሞም መጻፍ ልዩ መለያቸን ያደረግነው ኢትዮጵያዊያን ! ትርክቱን ከስንኙ ለማስተካካልን ተነሳን፡፡
ካይረባ ጓደኛ ይሻለኛል ዓባይ….ይሻላል ተከዜ፣
በዜት እንሻገር ………. ያሰኛል ሁል ጊዜ ፡፡
እናም የዓባይን ጓደኝነት ወደ አብራክ ክፋይ ልጅነት ለማሳድግ፣ በየጋራ ማእድ መጋራቱ ሳይዘነጋ አስጨናቂነቱን ለጠላቶቻችን ለማድረግ፣ ለመሻገሪያ ድልድይ ለማደሪያ ግድብ ልንሰራለት በወርሃ መጋቢት በሀያ አራተኛውም ቀን 2003 ዓ.ም ሆ! ብለን ተነሳን፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ በቀድሞ ርዕሰ መንግሥት አቶ መለስ ዜናዊ በኩል ጉባ ላይ አሳረፍን ፡፡
ይህ ዜና ለመላውና ለትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጭምር ብርቅና ድንቅ ቢሆንም ቅሉ ለጸሐፌ ተውኔቱ ጌትነት እንየው ግን እጅግም ልዩ ነበር፡፡
ስምን መልአክ ያወጣዋል እንዲሉ፤ የኪነ ጥበብ ጌታው ጌትነት ፤ አንድም የካርቱም ቁጭቱን ሲቀጥልም የሕዝቡን የአንድነት ስሜት እያጣቀሰ ብሶቱን ደግሞም ተስፋውን እንዲህ ሲል ከተበው፡-
ዓባይ ሐረግ ሆነ ከደም የወፈረ!
ለአዕላፍ ዘመናት ስንት ታሪክ ሰርቶ
ስንት ትውልድ አይቶ
ስንት ዓመት ተጉዞ እዚህ የደረሰው
ግዮን ስረ ብዙው
ዓባይ ስመ ብዙው
ናይል ገጸ ብዙው
የፈለቀበቱን የቃልኪዳን ስሩን መሬቱን ፈንቅሎ
ጥቁር አፈር አዝሎ
ሀገር አንጠልጥሎ
ውሃን አፈር ጭኖ ከሰው ቋት ማፍሰሱን
የወንዝ እንባ ሆኖ ሀገር ማስለቀሱን
በሀዘን በቁጭት የሀገር ፊት መጥበሱን
አንጀት መበጠሱን….
በሀገር ግፍ መዋሉን መበደሉን ትቶ
ባለፈ ተግባሩ በጎደፈ ስሙ አፍሮ ተጸጽቶ
በጊዜ ንስሃ ከዘመናት መርገምት ከበደሉ ነጽቶ
ከቆየ ልማዱ ከኖረ ምግባሩ ከባህሪው ወጥቶ
ውሃነቱን ትቶ
ወንዝነቱ ቀርቶ
እንዳንዳች ምትሀት ከቃልኪዳን ስሩ እየተመዘዘ
በአንድ የስሜት ግለት በአንድ የስሜት ሲቃ
ሀገር ጫፍ እስከ ጫፍ ሰቅዞ እየያዘ
ትውልድን ከታሪክ ታሪክን ከሀገር ስቦ እያዋደደ
አስማምቶ እያሰረ
ስሩ የጠለቀ
ግብሩ የረቀቀ
ውሉ የጠበቀ ዓባይ ሐረግ ሆነ ከደም የወፈረ
ይሄው ከዓይናችን ስር ዘመን መሰከረ
ይሄው ከእጃችን ላይ ግዮን ተቀየረ
ከእንግዲህ ባገሩ ሳቅ እና መስኖ እንጅ እንባ ሆኖ ላይገርፍ
ከእንግዲህ ላገሩ እጁ ላይታጠፍ
ጸጋው ላይገፍ
ግቱም ከቶ ላይነጥፍ
ከእንግዲህ ፍቅር እንጅ ሸፍጥ እና ድለላ ስሩን ላያስረሱት
ከእንግዲህ ምክር እንጅ ብረት እና ሴራ ውሉን ላያስረሱት
ያገር ውርስ እና ቅርስ እራት እና መብራት
ዋስ ጠበቃ ሊሆን መከታ እና ኩራት
“የሀገር ውርስና ቅርስ ራትና መብራት፣
ዋስ ጠበቃ ሊሆን ክብርና ኩራት
ይኸው በአዲስ ዘመን አዲስ ቃል ዘመረ
ከራሱ ታረቀ ካፈሩ መከረ
ለሀገሩ ቆመ በሀገሩ አደረ
ዜማና ቅኝቱ ረገደ ምቱ
ከጊዜ ከትውልድ ከሀቅ ሰመረ
ሃገርን ባንድ ነዶ ባንድ ልብ አሰረ
ይኸው ካይናችን ስር ከእውነት የነጠረ ከእምነት የጠጠረ
ዓባይ ሃረግ ሆነ ከደም የወፈረ፡
የአንድ ወንዝ ልጅ ሁሉ ይህን የዓባይ ሀረግ ከእምነትህ ጋር ቋጥረህ
ከጋራ አንገት መድፋት ከጋራ መሳቀቅ ከጋራ አፍረት ወጥተህ
በያለህበቱ በየዓለማቱ ጥግ በአንተነትህ ኮርተህ
አንተ ማነህ ሲሉህ
ከወዴት ነህ ሲሉህ
በሙሉ ራስነት አንገትህን አቅንተህ
ድምጽህን ከፍ አድረገህ
ደረትህን ነፍተህ
የዓባይ ልጅ ነኝ እኔ
ጦቢያ ናት ሀገሬ በል አፍህን ሞልተህ….
አሁን ቁጭትና ቁዘማው አልፏል፤ እንደዛትነውም የግድቡ የፋይናንስ ምንጭም፣ መኃንዲስም፣ ግንበኛም… እኛው ሆነን በሕዝብ እና የመንግሥታት ቅብብሎሽ ታላቁን ገድል በድል ተወጥተናል፡፡
ይህ በመሪዎች መቀያየር ያልተለወጠው ዓባይን በፍትሓዊነትና በጋራ የመጠቀም ኢትዮጵያዊ ህልም ግቡን መትቶ በርዕሰ መንግሥት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኩል ዓባይ-አባይ ከመሆን አልፎ ታማኝ የብርሃንና የኃይል ምንጭ ሆኗል!
እናም እንደከያኒው ሁላ አዎን የዓባይ ልጆች ነን! ታሪክ የቀየርን ስንል ደረታችንን ነፍተን፤ አንገታችንን ቀና አድርገናል፡፡
በአስማረ ቸኮል