Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ልዑክ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የተላከ መልዕክት ለደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት አደረሰ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑክ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተላከ መልዕክት ለደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት አድርሷል።

በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ የተመራው ከፍተኛ ልዑክ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ልዩ አማካሪ ግርማ ብሩ እና ሌሎች ከፍተኛ ኃላፊዎችን የያዘ ነው።

ልዑኩ መልዕክቱን ባደረሰበት ወቅት የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን መካከል ያለውን ታሪካዊና ጠንካራ ግንኙነት ለማስቀጠል ቁርጠኛ ናቸው ሲሉ አቶ አሕመድ ሺዴ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የሀገራቱን ህዝብ የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የኢኮኖሚ ትብብሮች ላይ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል።

ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በበኩላቸው ለደረሳቸው መልዕክት አመስግነው፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት ለማሳደግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

ሁለቱ ወገኖች የኢኮኖሚ ትብብርን ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የመከሩ ሲሆን የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ እና የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ላይ በትኩረት ለመስራት ውይይት አድርገዋል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በደቡብ ሱዳን የፋይናንስ ተቋማት መካካል ትብብርን ለማጎልበት እና የባንክ ሴክተሩን ለማሳደግም በትብብር እንደሚሰሩ ተገልጿል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያን፣ ደቡብ ሱዳንን እና ጂቡቲን የሚያገናኝ የትራንስፖርት ኮሪደር በመፍጠር የንግድ እንቅስቃሴን ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.