ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመከላከል በአይበገሬነት መስራት ይገባል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በወንጀል ድርጊት የተገኘ ኃብትን ህጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመከላከል በጋራ እና በአይበገሬነት መስራት ይገባል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
25ኛው የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ኃብትን ህጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን የመከላከል ቡድን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ እየተካሄደ ነው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመድረኩ እንዳሉት፤ ስብሰባው በጋራ በመቆም ለጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት እና ህብረተሰቡን ከጉዳት ለመጠበቅ ያለውን ቁርጠኝነት ይናገራል።
በተጨማሪም በቀጣናችን ልማትን የማስፋፋት መልዕክትን የሚያስተላልፍ መሰባሰብ ነው ብለዋል።
በወንጀል ድርጊት የተገኘ ኃብትን ህጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀል በቴክኖሎጂ ተደግፎ የሚፈጸምና በፍጥነት እየተስፋፋ ያለ ድንበር ተሻጋሪ ችግር መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም የዜጎቻችንን ሰላም እና እምነት እየቀማ የሚገኝ ለአፍሪካ አውዳሚ የሆነ ነው ብለዋል።
ከእያንዳንዱ የሚሰረቅ ገንዘብ ጀርባ ትምህርቱን የተቀማ ህጻን፤ ህክምና ማግኘት ያልቻለ ህመምተኛ፣ መሰረተ ልማት ያልተሟላለት ማህበረሰብ አለ ነው ያሉት።
እያንዳንዱ ጥፋት ሕዝባችን ነገ መድረስ ወደሚገባው እንዳይደርስ ወደ ኋላ ይጎትተናል ሲሉም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ኃብትን ህጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀል መከላከልን የሪፎርም አጀንዳዋ ዋና ማዕከል አድርጋ ብሔራዊ ኮሚቴ በማቋቋም እየሰራች እንደሆነ ጠቁመዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የገንዘብ ደህንነት አገልግሎት በአዲስ እንዲደራጅ መደረጉን ገልጸው፤ የፍትህ እና የሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አቅም እንዲጎለብት፣ የተቆጣጣሪዎች ውጤታማነት እንዲያድግ እና የግሉ ዘርፍ እንዲጠናከር እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በጋራ በመሥራት፣ እርስ በርስ በመገማገም፣ እውቀትን በመጋራት የሚስተዋሉ ክፍተቶችን መሙላት እንደሚቻል እና ውጤታማ የምንሆነው በጋራ እና በአይበገሬነት መስራት ሲቻል ነው ብለዋል።
ስራው ከአፍሪካም በመሻገር በዓለም ዙሪያ ሁሉ ጥረቶቻችንን ማስተሳሰር ያስፈልጋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር አጋርነት መፍጠር፣ ትግሉን የተቀናጀ ማድረግ፣ መረጃዎችን መለዋወጥ፣ እርስ በርስ መረዳዳት እና በድንበሮች አካባቢ መተማመንን መፍጠር ይገባል ብለዋል።
ስራው ከባድ እና ፈታኝ እንደሆነ እና ጉዳዩ የኢኮኖሚ ተልዕኮ ብቻ ሳይሆን የሞራል ተጠያቂነትን ለመወጣት የሚሰራ በመሆኑ ኢትዮጵያ የድርሻዋን በሚገባ ትወጣለች ሲሉ አረጋግጠዋል።
በለይኩን አለም
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!