Fana: At a Speed of Life!

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ ትስስር …

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ ትስስር ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያደርግ ግድብ ነው አሉ፡፡

ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሀይል የሚያመነጨው ግድቡ ባለው ጂኦፖለቲካዊ አቀማመጥ ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ትስስር በማጠናከር ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተማራማሪ ጥላሁን ሊበን ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ የቀጣናውን ትስስር ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነች ትገኛለች።

ከእነዚህ ተግባራት መካከል በኢነርጂ የማስተሳሰር ጥረት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ የህዳሴ ግድቡ ለዚህ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በርካታ ሀገራት በኢነርጂ ለማስተሳሰር የሚያስችል አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

ይህም የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ ለሆነው ነፃ የንግድ ቀጣና ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ነው ያስገነዘቡት፡፡

በኒው ጀነሬሽን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እና ተመራማሪ ቻን ዮም (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ግድቡ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ኩራት ነው ብለዋል፡፡

የግድቡ ፕሮጀክት በራስ አቅም እውን መሆኑ ለሌሎች ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው፤ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨት ባለፈ ለዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጥሩ ሌሎች ጠቀሜታዎች እንዳሉት አንስተዋል።

ለአብነትም በዓሣ ማምረት እና በቱሪዝም ዘርፍ ሰፊ የስራ ዕድል እንደሚፈጠር አንስተዋል።

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.