Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን – ጎሮ- ቪአይፒ አየር መንገድ ኮሪደር ያካተታቸው ሥራዎች…

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን – ጎሮ- ቪአይፒ አየር መንገድ ኮሪደር ልማት የአዲስ አበባ ከተማን ውብ ከማድረግ ባለፈ ለነዋሪዎች ሰፊ የሥራ እድል ፈጥሯል አሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
የአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን – ጎሮ- ቦሌ አየር መንገድ ቪአይፒ ተርሚናል ኮሪደር ልማት በዛሬው ዕለት ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የሁል ጊዜ ህልማችን እውን የሚሆነው በየዕለቱ፣ በየሰዓቱ፣ በየደቂቃው ያለዕረፍት በመስራታችን እና በፈጣሪ እርዳታ ነው።
የኮሪደር ልማቱ አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከልን ከቦሌ ኤርፖርት ቪአይፒ ተርሚናል የሚያገናኝ፣ ከአንበሳ ጋራዥ – ጃክሮስ ጐሮ እና በኮሪደር አንድ ከተሰራው ቦሌ ኤርፖርት መገናኛ ሲኤምሲ ጋር የሚገጥም ነው ብለዋል።
የኮሪደሩ አጠቃላይ ስፋት ከ290 ሄክታር በላይ ሲሆን÷ 12 ነጥብ 74 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዲሁም 29 ነጥብ 446 ኪ.ሜ የሚረዝም የእግረኛ መንገድ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም 15 ነጥብ 27 ኪሎ ሜትር የብስክሌት መንገድ፣ ከ550 በላይ ታክሲና ባሶችን የመያዝ አቅም ያላቸው 5 የባስና የታክሲ ተርሚናሎች አሉት፡፡
ከ800 በላይ መኪኖችን የመያዝ አቅም ያላቸው 4 ፓርኪንግን ጨምሮ ታክሲና ባስ መጫኛና ማውረጃ 17 ቤይ ተገንብቶለታል።
ኮሪደሩ 5 ኪሎ ሜትር የወንዝ ዳርቻ ልማት እና 2 ድልድዮች እንዲሁም 12 ኪ.ሜ የጎርፍ መውረጃ ቱቦ ዝርጋታን ጨምሮ 3 ነጥብ 6 ኪ.ሜ የመጠጥ ውሃ ዝርጋታ እና 669 የመንገድ ዳር መብራቶች ተሰርቶለታል።
ትላልቅና መካከለኛ ካፌዎች ፣ 41 መጸዳጃ ቤቶች፣ 9 የህጻናት መጫወቻ ቦታዎች እና 7 የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎችን ጨምሮ 4 ፕላዛዎች እና 130 ሄክታር የሚሸፍን የወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ ልማትን አካትቷል።
የኮሪደር ልማቱ ለነዋሪዎች ሰፊ የስራ እድል የፈጠረ፣ ፅዱ፣ አረንጓዴ እና ምቹ የመኖሪያ አካባቢ የፈጠረ፣ አካታች እና ሁሉንም ሰው ከልማቱ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡
ከ320 በላይ ህንፃዎች እድሳት በማድረግ እና ከ350 በላይ የንግድ ሱቆች በመክፈት የንግድ እንቅስቃሴው በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ያደርጋልም ነው ያሉት፡፡
የመንገድ መጨናነቅን ችግር በመፍታት የትራንስፖርት ፍሰቱን የሚያቀላጥፍ እና የተለያዩ የአገለግሎት መስጫዎችን ያሻሻለ ውጤታማ ሥራ እንደሆነ መጥቀሳቸውንም የከተማው ኮሙኒኬሽን ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.