Fana: At a Speed of Life!

መንግስት የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም በቁርጠኝነት እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግስት የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም በቁርጠኝነት እየሰራ ነው አለ የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን።
ኮሚሽኑ እና የአማራ ክልል መንግስት በጋራ ያዘጋጁት የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና በጠዳ ማዕከል በዛሬው ዕለት ተጀምሯል፡፡
የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር ብ/ጄ ደርቤ መኩሪያ በዚህ ወቅት÷ በሀገር አቀፍ ደረጃ 74 ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ማቋቋም መቻሉን ተናግረዋል።
በሁለት ዓመት ውስጥም ኮሚሽኑ 371 ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ እየሰራ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡
በአማራ ክልል የመልሶ ማቋቋም ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና እስካሁንም ከ11 ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች በተሃድሶ እንዲያልፉ መደረጉን አስታውሰዋል።
በክልሉ በሶስት ማዕከላት ከ6 ሺህ በላይ ለቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡
ከስልጠናው በኃላም መንግሥት በምህረት የገቡ ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋምና የመደገፍ ሥራ እንደሚያከናውን አስረድተዋል።
የአማራ ክልል ፓሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም መንግስቴ በበኩላቸው ÷መንግሥት የጀመራቸውን የሰላም አማራጮች ይበልጥ በማስፋት ለክልሉ ዘላቂ ሰላም መረጋጋጥ ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት ብለዋል።
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ያነጋገራቸው የቀድም ታጣቂዎችም መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀበለን ሰላማዊ የትግል አማራጭን ምርጫችን አድርገናል ነው ያሉት።
በምናለ አየነው
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.