Fana: At a Speed of Life!

በለነገዋ የሴቶች ተሀድሶና ማበልፀጊያ ማእከል የሰለጠኑ 810 ሰልጣኞች ተመረቁ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በለነገዋ የሴቶች ተሀድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ለሶስተኛ ዙር በተለያዩ ሞያዎች ሲሰለጠኑ የቆዩ ሰልጣኞች ተመርቀው ወደ ስራ ተሰማርተዋል፡፡

የሰልጣኞችን ምርቃት አስመልክተው ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት፣ማዕከሉ ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ተጋልጠው ጎዳና የወደቁ እና ለሴተኛ አዳሪነት የተጋለጡ ሴቶችን ከጎዳና በማንሳት በተለያዩ ክህሎቶች በማሰልጠን ወደ ስራ እያሰማራ ይገኛል ብለዋል።

የዛሬውን ጨምሮ ካሁን በፊት ስልጠና ወስደው ወደ ስራ የተሰማሩ ሴቶች ቁጥር 1 ሺህ 692 መድረሱን በመጥቀስ፣ለችግር ተጋላጭ ሴቶችን አሰልጥኖ ወደ ስራ ማሰማራት ከተማ አስተዳደሩ በትኩረት እያከናወነው የሚገኝ ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ሴት እህቶቻችን እነሱ ባልፈጠሩት ችግር ለመራር የህይወት ፈተና ሲጋፈጡ፣ ሲወገዙ፣ ሲገፉ፣ በረንዳ ሲወድቁ  እንዲሁም ለአስከፊው የሴተኛ አዳሪነት ህይወት ሲጋለጡ ይስተዋላል ያሉት ከንቲባዋ÷ የችግሩ ዋነኛ ምንጭ እነሱ ሳይሆኑ ድህነት እና ኋላቀርነት ነው ብለዋል።

ችግሩን ከስሩ መንቀያ ብቸኛው መንገድ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን ማድረግ መሆኑን ጠቁመው፣ለዚህም ከተማ አስተዳደሩ ሌት ተቀን መስራቱን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

ተመራቂዎች በማዕከሉ ቆይታ ያካበቱትን እውቀት፣ ክህሎት እና መልካም ስነ ምግባር በስራ ላይ በመተግበር መልካም ዜጋ እንዲሆኑ እና በተሰማሩበት ስራ ውጤታማ እንዲሆኑ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ይህንን መልካም ተግባር በእውቀት፣ በሞያ ፣ በሀብት ድጋፍ ላደረጉ ባለድርሻ አካላት፤ ባለሀብቶች እና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ምስጋና ማቅረባቸውን ከተማ አስተዳደሩ ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.