ለ9 ዓመታት በወር ደመወዙ ቦንድ የገዛው የመንግስት ሰራተኛ…
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለ9 ዓመታት በወር ደመወዙ ቦንድ የገዛው የመንግስት ሰራተኛ አቶ ራያ ጀማል፡፡
የህዳሴው ግድብ ግንባታ የመጀመሩ ሰበር ዜና ካስደሰታቸውና የራሴን አሻራ በግድቡ ላይ ማሳረፍ አለብኝ ብለው ከተነሱ ኢትዮጵያዊያን መካከል አንዱ ነው አቶ ራያ ጀማል፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በየም ዞን የመንግስት ሰራተኛ የሆነው ራያ ጀማል ለ9 ዓመታት በወር ደመወዙ ቦንድ በመግዛት የራሱን አሻራ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግብ ላይ አኑሯል።
ራያ ጀማል ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበረው ቆይታ የየም ዞን መንግስት ሰራተኞች እስከ 9ኛው ዙር በወር ደመወዛቸው ቦንድ መግዛታቸውን አስረድቷል፡፡
ዛሬ ላይ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ተጠናቆ በህይወት ዜናውን መስማት በመቻሌ ዕድለኛ ትውልድ አድርጎኛል ያለው አቶ ራያ በህይወት እስካለው የሀገርን ገፅታ ለሚቀይሩ ፕሮጀክቶች የበኩሌን ከማበርከት አልቆጠብም ብሏል።
አቶ ራያ በመንግስት ስራ የማገለግለው የየም ህዝብ እና አጠቃላይ የመንግስት ሰራተኞች ለግድቡ ሀብት ለማሰባሰብ ያደረጉትን ጥረት አለማመስገን አይቻልም ነው ያለው፡፡
ዛሬ ላይ የራሴን አሻራ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ማዋል በመቻሌ ከመላው ኢትዮጵያዊ ጋር በኩራት እቆማለሁ በማለት ተናግሯል፡፡
በተካልኝ ኃይሉ