Fana: At a Speed of Life!

የከተማችን ሰላም በማንኛውም እኩይ ተግባር እንዳይደናቀፍ አድርገናል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሰላም ሰራዊትን ከሕዝባችን መካከል እየመለመልን የከተማችንን ሰላም በማንኛውም እኩይ ተግባር እንዳይደናቀፍ አድርገናል አሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ።

በመዲናዋ በንድፈ ሐሳብና በመስክ የሰለጠኑ የ5ኛ ኮርስ አዲስ ምልምል የሰላም ሠራዊት አባላት በዛሬው ዕለት ተመርቀዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ፥ ሰላምን ማጽናት እና መንከባከብ የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የሰላም ሰራዊትን ከሕዝባችን መካከል እየመለመልን የከተማችንን ሰላም በማንኛውም እኩይ ተግባር እንዳይደናቀፍ አድርገናል ነው ያሉት።

የዛሬ ተመራቂዎችን ጨምሮ 275 ሺህ የሰላም ሰራዊት አባላት ለሰላም ግንባታ፣ ለኢኮኖሚ ፈጣን ለውጥና ለማህበራዊ እንቅስቃሴ ለሚያበረክቱት አስተዋፅኦም አመስግነዋል፡፡

የሰላም ሰራዊቱ አባላት ጉልበታቸውን፣ እውቀታቸውን እና ጊዜያቸውን በነጻ ሰጥተው የሚያገልግሉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫና ዋነኛ የዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗን ያወሱት ከንቲባዋ ፥ በቀጣይ ቀናት ለሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች ስኬታማነት በኃላፊነት አገልግሎት መስጠት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የሰላም ሰራዊቱ አባላት የከተማዋን ዓለም አቀፍ ተፅእኖና ለዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ያላትን ተመራጭነት በሚያጸና አግባብ በትህትና እና በፍቅር እንዲያስተናግዱ አስገንዝበዋል፡፡

ተመራቂ የሰላም ሰራዊት አባላት ከሰላም ወዳዱ ሕዝብ ጋር በመሆን ኃላፊነታቸውን በሚገባ እንዲወጡ ማሳሰባቸውንም ከተማ አስተዳደሩ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.