የወርቅ ምርት እና የመንግስት ትኩረት
አዲስአበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግስት በማዕድን ዘርፍ በተለይም በወርቅ ምርት ላይ ያደረገው ማሻሻያ እና የትኩረት አቅጣጫዎች ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገቡ መጥተዋል።
ኢትዮጵያ ካሏት የማዕድን ጸጋዎች አንዱ ወርቅ ቢሆንም ዘመናዊ የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካዎች በስፋት ባለመኖራቸው ምክንያት የዘርፉ አስተዋጽኦ ዝቅተኛ ሆኖ ቆይቷል።
ይሁን እንጂ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተሰጠው ትኩረት ከዋና ዋና ኢኮኖሚ ምሰሶዎች መካከል አንዱ በሆነው የማዕድን ዘርፍ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል።
በዚህ ረገድ የወርቅ ማዕድን በተሰጠው ትኩረት ልክ ውጤት አምጥቷል።
በኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ተመራማሪው ከተማ አብዲሳ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ ብሔራዊ ባንክ የወርቅ ግብይትን በተመለከተ ያወጣው መመሪያ እንዲሁም እየተገነቡ ያሉ ዘመናዊ የወርቅ ማምረቻዎች መንግስት ለዘርፉ ትኩረት መስጠቱን ያሳያሉ።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በዋናነት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት እና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ማሳደግ መሆኑን ገልጸው፤ ማሻሻያው ወርቅ እና ሌሎች ማዕድናት በከፍተኛ ደረጃ እንዲመረቱ ማስቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
የወርቅ ማዕድንን በዘመናዊ መንገድ ለማምረት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ቀደም ሲል የነበረውን ኋላቀር የአመራረት ዘዴ እንዲቀንስ አድርጓል ብለዋል።
ቀደም ሲል በህገ ወጥ መንገድ ይዘወር ነበር ያሉት ተመራማሪው፤ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው የገበያ ትስስር መመሪያ ህገ ወጥነት እንዲቀነስ በማድረግ መንግስት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ በአግባቡ እንዲያገኝ አስችሏል ነው ያሉት።
በፈረንጆቹ 2021/22 ኢትዮጵያ ወርቅን ወደ ውጭ በመላክ ያገኘችው የውጭ ምንዛሪ 672 ሚሊየን ዶላር ብቻ እንደነበር አስታውሰው÷ ማሻሻያውን ተከትሎ በ2017 በጀት ዓመት 37 ቶን የወርቅ ምርት ለውጭ ገበያ መቅረቡን ጠቅሰዋል፡፡
መንግስት በዘርፉ ያደረጋቸው ማሻሻያዎች የወርቅ ምርትን ከማሳደግ እና የኢኮኖሚ እድገትን ከማሻሻል በተጨማሪ ከፍተኛ የስራ እድል እንዲፈጠር ማድረጉን ነው ተመራማሪው የተናገሩት፡፡
በሚኪያስ አየለ