በአማራ ክልል በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዘርፍ ውጤታማ ሥራ ተከናውኗል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ በክልሉ በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዘርፍ ውጤታማ አፈጻጸም ተመዝግቧል አለ።
የቢሮው ሃላፊ መልካሙ ፀጋዬ ÷ አማራ ክልል አብያተ መንግሥታትና ቤተ እምነቶች በብዛት ያሉበት በመሆኑ የቅርስ ጥበቃና ጥገና ሥራ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል።
በዚህም በተጠናቀቀው 2017 በጀት ዓመት በክልሉ ለተለያዩ ቅርሶች የጥገና ሥራ መከናወኑን ነው የገለጹት፡፡
ለኪነ ሕንጻና ሌሎች ቅርሶች እድሳት የሚውለውን የኖራ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ግንባታ በክልሉ ውስጥ ማስጀመር መቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡
ፋብሪካው በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት መጨረሻ ላይ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመው ÷ ይህም ለዘርፉ የጎላ ጠቀሜታ ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡
የጎብኚዎችን እርካታ በማሳደግ የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም የመዳረሻ ልማት ሥራዎች ላይ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡
የቱሪዝም አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን አቅምና ተደራሽነት ለማጠናከር ከስልጠና ጀምሮ ሌሎች ድጋፎች እየተደረጉ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የቱሪዝም ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥን በቴክኖሎጂ ለማገዝ ከክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር የተሳለጠ የቱሪዝም አገልግሎት አስተዳደር ሥርዓት እየለማ ነው ብለዋል፡፡
በደሳለኝ ቢራራ