Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ከዘመን ጋር የዘመኑ የጸጥታ ተቋማት እየገነባች ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከዘመን ጋር የዘመኑና በሕገ መንግሥታዊ ዕሴቶች ላይ የተመሰረቱ የጸጥታ ተቋማት እየገነባች ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ ከጸጥታ ተቋማት አመራሮች ጋር ሲደረግ የነበረው ውይይት በዛሬው ዕለት ተጠቃልሏል ብለዋል፡፡

የጸጥታ ተቋማት ወትሮ ዝግጁነት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስከበር በሚያስችል ደረጃ ላይ መድረሱ በውይይቱ ላይ ተገምግሟል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ ከዘመን ጋር የዘመኑና በሕገ መንግሥታዊ ዕሴቶች ላይ የተመሰረቱ የጸጥታ ተቋማት እየገነባች መሆኑን ጠቅሰው፥ መቼም፣ የትም እና ለምንም ዓይነት ሁኔታ ዝግጁ የሆኑ የጸጥታ ተቋማት ግንባታ የዘወትር ተግባር ለማድረግ አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል፡፡

የአሻጥር፣ የከተማና የገጠር ውንብድና፣ የኮንትሮባንድ፣ የሙስና፣ ሕገ ወጥ የሰዎችና የገንዘብ ዝውውርና መሰል ወንጀሎችን በመከላከልና በመቆጣጠር የሕዝቡን ሰላም ማስከበር እንደሚገባ በውይይቱ ላይ በስፋት ተነስቷል፡፡

የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ለማደናቀፍ በማኅበራዊ ሚዲያ የሽብር ተግባር የሚፈጽሙ አካላትን በተለይም በሳይበር ቴክኖሎጂ የመከታተልና የመቆጣጠር ሥራዎች ይበልጥ ሊጠናከሩ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጂኦ ፖለቲካዊ ኩስመና ማክተሙንና ቁመናዋ እየተስተካከለ መምጣቱን ጠቅሰው፥ የጸጥታ ተቋሞቻችን የሀገሪቱን ዳር ድንበር፣ ሉዓላዊነት፣ ነጻነት፣ ሰላም እና ደኅንነት ብሎም የብልጽግና ጉዞ ለማስከበር በሚችሉበት ዐቅምና ዐቋም ላይ ናቸው ብለዋል፡፡

የጸጥታ ተቋማት ዋና ተልዕኮ ሰላምን ማጽናት መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይሄንኑ ወትሮ ዝግጁነት ይበልጥ በማጠናከር፣ የውስጥና የውጭ ችግር ፈጣሪዎችን አደብ አስገዝቶ፣ ሰላምን በሚያጸና ልክ መቀጠል እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.