ሥራን በብቃትና በጥራት መከወን ጊዜው የሚጠይቀው አርበኝነት ነው – ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሥራን በብቃትና በጥራት መከወን ጊዜው የሚጠይቀው አርበኝነት ነው አሉ ሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር (አይኤስኦ 9001-2015) የጥራት ሥራ አመራር ትግበራ በመፈጸም ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያገኘ ሲሆን፥ የምስክር ወረቀት አሰጣጥ ሥነሥርዓት እየተካሄደ ይገኛል።
ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የዘርፉን ተልዕኮ ማሳካት የሚያስችሉ የለውጥ ስራዎች ሲተገብር ቆይቷል።
በጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት የተቀመጡ መስፈርቶችን ለማሟላት በትጋት ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው፥ የለውጡን መሳሪያዎች አሰናስኖ በመጠቀም ተጨባጭ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።
ዓለም አቀፍ ዕውቅናው ተቋሙን ለበለጠ ትጋት የሚያነሳሳ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፥ የቴክኒክና ሙያ ሥራን ጨምሮ ተቋማቸው የሚያከናውናቸውን ተግባራት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ሥራን በብቃትና በጥራት መከወን ጊዜው የሚጠይቀው አርበኝነት መሆኑን ጠቁመው፥ የኢትዮጵያ ተቋማት ጥራትን የመለያ መንገዳቸው በማድረግ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና ተቀባይነት እንዲኖራቸው በትጋት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በቀጣይም ወጥነት ያለው አገልግሎት በመስጠት የደንበኞችን እርካታ ለመጨመር ሁሉም እንዲተጋ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።