Fana: At a Speed of Life!

የአፋር ህዝብ የሀገሩን ሉአላዊነትና ክብር ለማስቀጠል የድርሻውን ይወጣል – አቶ አወል አርባ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፋር ህዝብ የሀገሩን ሉአላዊነትና ክብር ለማስቀጠል የድርሻውን ይወጣል አሉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፡፡

በክልሉ ሰመራ ከተማ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ‘ጽኑ መሰረት ብርቱ ሀገር’ በሚል መሪ ቃል እየተከበረ የሚገኘው ጳጉሜን 1 የጽናት ቀን ላይ አቶ አወል ባስተላለፉት መልዕክት፤ የአፋር ህዝብ የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ሌሎች የፀጥታ ተቋማት የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስቀጠል እየከፈሉ ላለው መስዋዕትነት ትልቅ ክብር አለው ብለዋል፡፡

ጽኑ ሀገር መገንባት የሚቻለው በትውልድ ቅብብሎሽ በሚከፈል መስዋዕትነት መሆኑን ገልጸው÷ የአፋር ህዝብም ከፀጥታ ተቋማቱ ጎን በመቆም የሀገሩን ሉአላዊነትና ክብር በፅኑ መሰረት ላይ ለማስቀመጥ የድርሻውን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ ርዕሰ መስተዳድሩ እና የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ አስያ ከማል የሰንደቅ ዓላማ መስቀል ሥነ ሥርአት አከናውነዋል ።

የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የፌዴራል ፖሊስ አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡

በያሲን ኑር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.