ታላቁ የሕዳሴ ግድብ እውን እስከመሆን ድረስ ያገኘነው ስኬት የጽናታችን ውጤት ነው – አይሻ መሐመድ (ኢ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጸጥታና የደኅንነት ተቋማትን ከማዘመን ጀምሮ እስከ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እውን እስኪሆን ድረስ ያገኘነው ታላቅ ስኬት፣ የጋራ ዓላማችን እና ያላሰለሰ ጽናታችን ነው አሉ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር)።
ጳጉሜን 1 የጽናት ቀን ‘ጽኑ መሰረት፤ ብርቱ ሀገር’ በሚል መሪ ቃል በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተከበረ ይገኛል።
በዝግጅቱ ላይ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰን ጨምሮ የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)፣ ሚኒስትሮች፣ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት አመራሮች፣ የተለያዩ የስራ ሀላፊዎች፣ ከፍተኛ የመከላከያ ሰራዊትና የፌዴራል ፖሊስ አመራር አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ዛሬ የጽናት ቀንን ስናከብር ያለፉትን ድሎች ብቻ ሳይሆን፤ የወደፊቱን ተስፋዎቻችንን እየተቀበልን ነው ብለዋል።
ጽናት የሚመራን ኮምፓስ፣ የአንድነታችን ኃይልና መንገዳችንን የሚያበራልን ችቦ ነው ሲሉ መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የጸጥታና የደኅንነት ተቋማትን ከማዘመን ጀምሮ እስከ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ እውን መሆን ድረስ ያገኘነው ታላቅ ስኬት፤ የአንድነታችን፣ የጋራ ዓላማችን እና ያላሰለሰ ጽናታችን ውጤት መሆኑን በኩራት እናረጋግጣለን ነው ያሉት።
ለስኬቶቹ መንገድ የከፈቱት ጀግኖቻንን ድፍረት፣ የመስዋዕትነትና የማይናወጥ ጽናትን እናስታውሳለን፤ እናከብራለንም ብለዋል።
የዛሬው ዕለት ፈተናዎችን ሁሉ ወደ መልካም አጋጣሚ ቀይረን ኢትዮጵያን ወደ አዲስ የብልጽግና፣ የክብርና ዘላቂ ከፍታ ለማድረስ ቃል የምንገባበት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
እንደ ኢትዮጵያዊ የጀግኖቻችንን መንፈስ ተቀብለን ወደ ፊት ለመሻገር እንነሳ ያሉት ሚኒስትሯ፤ ፈተናዎችን ሁሉ ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር በተስፋ፣ በአንድነትና በዘላቂ ብልጽግና የተሞላ የወደፊት ዕድልን መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በአዲስ ተስፋ፤ በጽኑ መንፈስና በማይናወጥ አንድነት መቆም እንደሚገባ አስረድተው፤ ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግናና ታላቅነት የምታደርገውን ጉዞ በይበልጥ ከፍ የምታደርግበት አዲስ ምዕራፍ መጀመሩንም ገልጸዋል።
ሀገራችን በጽናት፣ በጥንካሬ፣ በክብር እና በስኬት ትደምቃለች፤ የሚል የጋራ ርዕይ ይዘን በይበልጥ በቁርጠኝነት እንትጋ ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።