የኅብር ቀን በኦሮሚያ ክልል እየተከበረ ነው
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኅብር ቀን “ብዝኃነት የኢትዮጵያ ጌጥ” በሚል መሪ ሀሳብ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡
በክልል ደረጃ በሻሸመኔ ከተማ እየተከበረ በሚገኘው በዓል ላይ ልዩ ልዩ ክዋኔዎች ቀርበዋል፡፡
የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ሰዓዳ አብዱራህማን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ዜጎች በአንድነት በመቆም የልማት ስራን በጋራ በመስራታቸው እንደ ሀገር ትልቅ የልማት ውጤት ተገኝቷል።
ኢትዮጵያ መልከ ብዙ ሀብቶችና እሴቶች ያላት፣ በአንድነት መኖርን የሚያወቁ ሀዝቦች መገኛ እንደሆነች ገልጸው ለሁሉ የምትሆን ኢትዮጵያን መፍጠር ተችሏል ነው ያሉት።
አንድ ስንሆን የተሻለ ማድረግ እንችላለን ያሉት አፈ ጉባኤዋ፥ ባለፉት 7 አመታት በርካታ የልማት ውጤቶች መገኘታቸውንና በአለም ላይ ተፅዕኖ መፍጠር እንደተቻለ አንስተዋል፡፡
አንድነትነ ወንድማማችነት እና አብሮነትን ማጠናከር እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
በክብረ በዓሉ ላይ የተሳተፉ አባ ገዳዎች ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በሰጡት አስተያየት፥ አንድነታችን ጥንካሪያችን በመሆኑ ከከፋፋይ ነገር ራሳችንን መጠበቅ አለብን ብለዋል።
የኢትዮጵውያን የጋራ ሀብት የሆነው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በመጠናቀቁ መደሰታቸውን ገልጸው፥ በቀጣይ አንድነታችንን በማጠናከር ልማታችንን ማፋጠን ይጠበቅብናል ነው ያሉት።
በመርሐ ግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ ተጋባዥ እንግዶችና የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
በብርሃኑ በጋሻው