Fana: At a Speed of Life!

ኤመራልድ በዳታ ሳይንስ የግል የድሕረ ምረቃ መርሐ ግብር አስጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2017 (ኤፍ ኤምሲ) ኤመራልድ ኢንትርናሽናል ኮሌጅ በዳታ ሳይንስ የግል የድሕረ ምረቃ መርሐ ግብር አስጀምሯል፡፡
ኮሌጁ በዳታ ሳይንስ፣ በኤምቢ እና በአመራር የትምህርት ዘርፎች በ2ኛ ዲግሪ የትምህርት መርሐ ግብር ያስተማራቸውን 184 ተማሪዎች ከፍተኛ የመንግሥት አካላት በተገኙበት በሂልተን ሆቴል አስመርቋል።
ኤመራልድ ኢንተርናሽናል ኮሌጅ ከተቋቋመ አራት አመት ያስቆጠረ ሲሆን ፥ በዳታ ሳይንስ እንዲያሰለጥን ከትምህርት ሚኒስቴር እውቅና ተሰጥቶታል፡፡
ኮሌጁ ዛሬ ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 57ቱ ሴት ተመራቂዎች መሆናቸው ነው የተገለጸው፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ፥ ተመራቂዎች ያገኙትን ታላቅ ስጦታ ወደ ተግባር በመቀየር ሀገራቸውን ለመለወጥ ሊጠቀሙበት ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የዲጂታል ዘመንን መሰረት ያደረገ ሥራ እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው ፥ ኤምራልድ ኮሌጅም ይህንን በተግባር አሳይቷል ነው ያሉት፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ ሂክማ ኸይረዲን በበኩላቸው፥ የትምህርት ተቋማት በቴክኖሎጂው ዘርፍ የሴቶች ቁጥር ከፍ አንዲል የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
መንግስት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከሚሰራቸው ዘርፈ ብዙ ሥራዎች በተጨማሪ የባለድርሻ አካላት የሚያከናውኑት ተግባር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ጠቅሰዋል፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዶች ባስተላለፉት መልዕክት፥ ኤመራልድ ኢንተርናሽናል ኮሌጅ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን በዳታ ሳይንስ የግል የድህረ ምረቃ መርሐ ግብር በማስጀመር ታሪክ መስራቱን አውስተዋል፡፡
ኮሌጁ ባመቻቸው የነጻ የትምህርት እድል ከ18 የመንግስት መስሪያ ቤቶች የመጡ መካከለኛና ከፍተኛ አመራሮችን በአመራር የትምህርት ዘርፍ ማስመረቁም ተጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.